ከይርጋለም የተቀናጀ ግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ባለፉት 11 ወራት የአቮካዶ ዘይት ምርት ወደ ውጭ በመላክ 3.6 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ መገኘቱ ተገልጿል።
የአካባቢውን የግብርና ምርቶች እሴት ጨምሮ ወደ ተለያዩ ገበያዎች ለማቅረብ የሚሰራው ፓርኩ፤ አሁን ላይ ከ136 ሺህ በላይ ከሚሆኑ የአካባቢው አቮካዶ አምራች አርሶ አደሮች ጋር ትስስር መፍጠሩን የሲዳማ ክልል ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኃይሉ የተራ ለኢቢሲ ገልጸዋል።
ከአምስት ዓመታት በፊት ወደ ሥራ የገባው የይርጋለም የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በውስጡ በተለያዩ የግብርና ምርቶች ማቀነባበር ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ይገኛሉ ተብሏል።
ፓርኩ ባለፉት አምስት ዓመታት ወደ ውጭ ከላካቸው ምርቶች 20 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ገቢ ማግኘቱን አቶ ኃይሉ አንስተዋል።

ከተለያዩ የዓለም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ወተትን ጨምሮ የተለያዩ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በማምረት የውጭ ምንዛሬን ለማዳን እየተሰራ መሆኑንም ዋና ሥራ አስፈፃሚው አክለው ተናግረዋል።
በፓርኩ እስካሁን ወደ ስራ ከገቡት 8 ኩባያዎች በቀጣዩ ዓመት በቡና፣ ሙዝ እና ኦቾሎኒ ማቀነባበር ላይ የሚሰሩ 3 ኩባንያዎችን ስራ ለማስጀመር ዝግጅት መደረጉን አቶ ኃይሉ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም ፓርኩ በ2018 ዓ.ም 12 አዳዲስ ኩባንያዎችን ወደ ስራ እንዲገቡ እየሰራ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ አራቱ የውጭ ድርጅቶች እንደሆኑ አስታውቋል።
በአስረሳው ወገሼ