Search

ኢትዮጵያ በሚገባት ልክ ያልተጠቀመችበት የቀርከሀ ሀብት

ሓሙስ ነሐሴ 08, 2017 109

ኢትዮጵያ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የቀርከሀ ሀብት ቢኖራትም፤ ከሚገኘው ምርት የሚጠበቀውን ያህል እየተጠቀመች አለመሆኗ ግን ይገለጻል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ዳውሮ ዞን የቀርከሀ ምርት በስፋት የሚገኝ ቢሆንም፤ ምርቱን ከፍ ወዳለ አገልግሎት የሚቀይር ፋብሪካ ባለመኖሩ ለቤት ስራ፤ለአጥር፤ ለከብት መኖ እና ለመሳሰሉት አገልግሎቶች ብቻ በመዋል ላይ ይገኛል።

ኢቢሲ በስቱዲዮ ይህንኑ ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ እንግዶችን ጋብዞ አነጋግሯል ።

በኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ልማት የቀርከሀ ኤክስፐርት የሆኑት አቶ አክሊሉ አየለ፥ በኢትዮጵያ 1.4 ሚሊየን ሔክታር መሬት አከባቢ ቀርከሀ ሽፋን መኖሩን ገልፀዋል።

በሀገሪቱ ካለው የቀርከሀ ሀብት አንፃር በፋብሪካ ደረጃ ፕሮሰስ የማድረጉ ሒደት ዝቅተኛ መሆኑንም ተናግረዋል።

ምርቱ ያለባቸው አከባቢዎች ላይ አጠቃቀሙን ከባህላዊ አሰራር በማውጣት እና ወደ ኢንዱስትሪ በማሸጋገር፤ የተለያዩ ምርቶችን ማምረት ይቻላልም ነው ያሉት ኤክስፐርቱ።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕራይዝ ጥናት አድርጎ በኢንዱስትሪው ለሚሰማሩ እና በመስራት ላይ ለሚገኙ ድርጀቶች ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሚገኝም ተናግረዋል።

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የአከባቢ ደን ሐብት ጥበቃ እና የአየር ንብረት ለውጥ ባለስልጣን ዳይሬክተር ሉቅማን አብዱልቃድር በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ካላት ከ 1ሚሊየን ሔክታር በላይ የቀርከሀ ምርት ሽፋን ሰፊው  የሚገኘው በቤኒሻንጉል ክልል መሆኑን ጠቅሰዋል። 

በፋብሪካ ደረጃ የምርት ሂደት በቂ የሆነ ሥራዎች ባይሰሩም ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ከ2.5 ሚሊየን በላይ ቀርከሀ ወደ ውጭ በመላክ ከ250 ሺህ በላይ ዶላር ገቢ ማገኘቱን ተናግረዋል።

በቀጣይ ምርቱን ከመላክ ይልቅ የተለያዩ እሴቶች ታክለውበት በወረቀት መልክ፣ በጣውላ እንዲሁም የተለያዩ መገልገያ መሳሪያዎችን በማምረት ኤክስፖርት ቢደረግ፤ ሀገሪቷን ተጠቃሚ የሚያደርግ በመሆኑ በዚህ ዘርፍ ለመስራት ለሚመጡ ባለሀብቶች በራችን ክፍት ነውም ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በንፍታሌም እንግዳወርቅ