Search

አዳዲስ ጉዳዮችን ይዞ ከ82 ቀናት በኋላ ዛሬ የሚጀመረው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ

ዓርብ ነሐሴ 09, 2017 148

የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ለሦስት ወር የቀረበ ጊዜ ረፍት ካደረገ በኋላ ዛሬ ከአዳዲስ ተጫዋቾች ጋር ብቻ ሳይሆን ከአዳዲስ ጉዳዮች ጋር ይመለሳል፡፡
ምሽት 4 ሰዓት ላይ በአንፊልድ ሊቨርፑል ከ ቦርንማውዝ የሚያደርጉት ጨዋተ ደግሞ የሊጉ መክፈቻ ሆኗል፡፡
ክለቦች በአዲሱ የውድድር ዘመን ጠንካራ ሆኖ ለመቅረብ በርካታ የአቋም መለኪያ ጨዋታዎችን ከማድረግ ጀምሮ ረብጣ ገንዘብ አውጥተው ተጫዋቾችን አስፈርመዋል፡፡
ክለቦች ካስፈረሟቸው ተጫዋቾች አንጻር ለዋንጫ የሚደረገው ፉክክር ከቀደሙት አመታት እጅግ ጠንካራ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ የሊጉ ሻምፒዮን ሊቨርፑል እስከ አሁን ከ280 ሚሊዮን ፓውንድ በላይ ወጭ አድርጎ ልዩነት ፈጣሪ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡
አርሰናል ለዓመታት ጥያቄ ሲነሳበት የነበረውን የፊት መስመር ችግር ለመፍታት ቪክቶር ጊዮኬሬሽን ጨምሮ ከአማካይ እስከ ተከላካይ አስፈርሟል፡፡
ባለፈው ዓመት አስቸጋሪ የውድድር ጊዜ ያሳለፈው ማንችስተር ሲቲ ከጥር የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ጀምሮ ራሱን በሚገባ አጠናክሯል፡፡
ረብጣ ገንዘብ አውጥቶ ከዋክብትን በመሰብሰብ የሚታወቀው ቼልሲ በዚህኛው የዝውውር መስኮት የለቀቃቸው ተጫዋቾች እንዳሉ ሆነው 8 ተጫዋቾች ወደ ምዕራብ ለንደን ወስዷል፡፡
በሊጉ 15ኛ ደረጃን ይዞ የጨረሰው ማንችስተር ዩናይትድ በተለይ የፊት መስመሩን ለማጠናከር ቤንጃሚን ሸሽኮ፣ ብሪያን ምቤሞ እና ማቲያስ ኩንሀን አስፈርሟል፡፡
ከሻምፒዮን ሽፑ ያደጉት እንደ ሰንደርላንድ አይነት ቡድኖች በሊጉ ለመቆየት እስከ 10 የሚደርሱ ተጫዋቾችን ሲያስፈርሙ ለዋንጫ ብቻ ሳይሆን በሊጉ ለመቆየት የሚደረገው ፉክክርም ቀላል እንደማይሆን ይገመታል፡፡
ባለፉት 25 ዓመታት በናይክ ኳስ ሲጫዎት የቆየው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በአዲሱ የውድድር አመት በፑማ ኳስ የሚጫዎት ሲሆን የግብ ጠባቂዎች የ8 ሰከንድ ህግ፣ ሰሚ አውቶሜትድ ኦፍሳይድ ቴክኖሎጂ፣ በጨዋታ መሀል ተቀይረው የሚወጡ ተጫዋቾችን ቃለ መጠይቅ ማድረግ እና ዋና ዳኞች የቫርን ውሳኔ በግልጽ መሳወቅ 380 ጨዋታዎች በሚደረጉበት ሊግ አዲስ የሚተገበሩ ህጎች ናቸው፡፡
ዛሬ በሚጀመርው መርሐ ግብር የሊጉ ሻምፒዮን ሊቨርፑል ምሽት 4 ሰዓት ላይ በሜዳው ቦርንማውዝን ያስተናግዳል፡፡ ክለቡን በተረከቡበት ዓመት የሊጉን ዋንጫ ያሳኩት አሰልጣኝ አርን ስሎት በተከታታይ ስኬታማ ለመሆን ዛሬ አጀማመራቸውን ማሳመር ይጠበቅባቸዋል፡፡
በክረምቱ የተጫዋቾች ዝውውር ሦስት ወሳኝ ተካለካዮቹን ያጣው ቦርንማውዝ ከሊቨርፑል ካደረጋቸው ያለፉት 12 ጨዋታዎች በ11ዱ ተሸንፏል፡፡
የመርሲሳይዱ ክለብ በቅርቡ በመኪና አደጋ ህይወቱን ላጣው ተጫዋቹ ዲየጎ ዦታ እና ወንድሙ አንድሬ ሲልቫ መታሰቢያ በማድረግ ረጅሙን ጉዞ የሚጀምርም ይሆናል፡፡
 
በአንተነህ ሲሳይ