Search

"ሰፊ እና ምቹ መንገድ ባለበት የፍጥነት ወሰን ምን ያደርጋል? ነዳጅ እና ጊዜስ ለምን ይባክናል?"

ዓርብ ነሐሴ 09, 2017 128

 

በአዲስ አበባ ከተማ ከተፈቀደው የፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር አሽከርካሪዎችን ለቅጣት ይዳርጋቸዋል።  

በሌላ በኩል አሽከርካሪዎች የተቀመጠውን ዝቅተኛ የተሽከርካሪ የፍጥነት ወሰን በመጠበቅ በሚያሽከረክሩበት ወቅት በተለይ በአንዳንድ አካባቢዎች ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ይፈጠራል።

ይህም አሽከርካሪዎች ተሳፋሪዎችን ከአሰቡበት መዳረሻ በወቅቱ ማድረስ እንዳይችሉ በማድረግ የበርካቶች የቅሬታ ምንጭ ሲሆን ይስተዋላል።

ይህን በተመለከተ ኢቢሲ ዶትስትሪም ያናገራቸው የመንገድ ደህንነትና መድህን ፈንድ አገልግሎት ዋና አስፈፃሚ አቶ ጀማል አባሶ፥ አሽከርካሪዎች ከተፈቀደላቸው የፍጥነት ወሰን በላይ ማሽከርከር እንደሌለባቸው ነው የተናገሩት።

"ሰፊ እና ምቹ መንገድ ባለበት የፍጥነት ወሰን ምን ያደርጋል? ነዳጅ እና ጊዜ ለምን ይባክናል?" የሚል ሀሳብ አሽከርካሪዎች በተደጋጋሚ እንደሚያነሱ ጠቅሰው፤ ሆኖም ግን የተቀመጠውን የፍጥነት ወሰን ጠብቆ ማሽከርከር እንደሚገባ ነው ያሳሰቡት። 

ዓላማውም በከተማዋ የትራፊክ አደጋ በሰው እና በንብረት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመከላከል ብቻ እንደሆነም ነው የገለፁት።

በፍጥነት መንገዶች እና ባለሁለት መስመር አስፋልቶች ሳይቀር የፍጥነት ወሰኑ ዝቅተኛ መሆኑ የትራፊክ እንቅስቃሴውን አዳጋች አድርጎታል የሚል ቅሬታም ይቀርባል።

አቶ ጀማል ለዚህ በሰጡት ምላሽ፥ አሽከርካሪዎች በነዚህ መንገዶች ሲያሽከረክሩ ሰዎች ድንገት ቢገቡባቸው ለመቆጣጠር አዳጋች በመሆኑ የፍጥነት ወሰኑን ዝቅ እንዲል መደረጉን ተናግረዋል።

መንገዱ ሰፊ መስሎ ቢታይም የህዝብ ቁጥሩ ያለማቋረጥ እያደገ በመሆኑ የፍጥነት ወሰኑ አደጋን ለመከላከል ትልቅ ጥቅም እንዳለው ገልፀዋል።

እንዲያም ሆኖ የፍጥነት ወሰኑን ጠብቆ ማሽከርከር ይፈጥረዋል ለተባለው የትራፊክ መጨናነቅ እና የጊዜ ብክነት በጥናት ላይ የተመሠረተ ተገቢ መፍትሔ ለመስጠት ውይይት እንደሚደረግበት ነው ዋና ሥራ አስፈፃሚው ለኢቢሲ ዶትስትሪም የተናገሩት።

በሜሮን ንብረት

#ኢቢሲ #ኢቢሲዶትስትሪም #አዲስአበባ #የፍጥነትወሰን