ከባህር በር አማራጭ መራቅ የሚያስከትላቸውን ችግሮች ለመፍታት በማሰብ ነበር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራትን ጉባዔ ማካሄድ የጀመረው፡፡
እ.ኤ.አ በ2003 ለመጀመሪያ ጊዜ በካዛኪስታን አልማቲ ከተማ የተካሄደው ጉባዔው የሀገራቱ የባህር ላይ ትራንስፖት እንዲመቻች እና የመተላለፊያ ኮሪደር እንዲያገኙ ብሎም ለባህር በር ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ እንዲከፍሉ በሚያስችላቸው ነጥቦች ላይ ያተኮረ ነበር፡፡
ይህንንም እንዲያጠናክር እን በአስተናጋጅ ከተማዋ የተሰየመው ‘የአልማቲ ዲክላሬሽን’ የተፈረመው፡፡
የስምምነቱ ነጥቦች እ.ኤ.አ ከ2003 እስከ 2013 ተግባራዊ እንዲሆን የተሰራም ነበር፡፡
በኋላም በሁለተኛው ጉባዔ ቪየና ተካሄደ ። በቪየና ስምምነት መሰረትም ሀገራትን እንዴት ማሳደግ እንደሚቻል በተለይም የንግድ ትስስራቸው እንዲጨምር ማድረግ’ ላይ ያተኮረ አጀንዳ ተነስቷል።
ጥሬ እቃ ከመላክ በውስጥ አቅም ማምረት እንዲቻል ፣ የድንበር ተሻጋሪ ንግድ እክሎችን መቅረፍ ብሎም ለችግሮች ፈጣን ምላሽ የመስጠት አቅምን ማጠናከር ላይ እንዲሰራም አቅጣጫ ያስቀመጠ ነበርል፡፡
‘የቪየና ስምምነት’ በዚህ መልኩ ተወልዶ እ.ኤ.አ ከ2014-2024 እንዲተገበር የተወሰነ እንደነበር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያሳያል፡፡
ቱርኪሚስታን ያስተናገደችው 3ተኛው የባህር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት ጉባዔ ደግም ሀገራቱ የባህር በር አማራጭ ስለሌላቸው የጂኦግራፊ እስረኛ መሆን እንደሌለባቸው ያነሳ ሆኖ አልፏል፡፡
ይህን ሀሳብ የሚያጠናክረው ‘የአዋዛ ዲክላሬሽን’ በተሳታፊ ሀገራት ተስፋ የተጣለበት መሆኑንም በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነት እና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈቲህ ማህዲ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
እ.ኤ.አ በ2024 ሃሳቡ ተጠንስሶ በ3ተኛው የተመድ ጉባዔ ላይ ተግባራዊነቱ የተመከረበት ‘የአዋዛ ዲክላሬሽን’ የሀገራቱ ተስፋ መሆኑን ምክትል ሰብሳቢው ይገልፃሉ::
የሳይንስና ቴክኖሎጂና ፈጠራን በማሳደግ የሀገር ውስጥ ምርታማነት መጨመር ብሎም ለገቢ ምርት የሚወጣውን የማጓጓዣ ወጪ መቀነስ አንዱ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የተፋጠነ የንግድ ትስስር እንዲፈጠር እና በሌሎች ሀገራት ፈቃድ ላይ እንዳይመሰረት ማድረግ በተለይም ይህ እንዲሆን የሚያስችል የመሰረተ ልማት ትስስር መፍጠር ላይ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር የፋይናንስ እና የቴክኒክ አተገባበር እገዛ ያለው መሆኑን በጉባዔው ተሳታፊ የነበሩት ዶ/ር ፈቲህ ለኢቲቪ ተናግረዋል፡፡
“ጂኦግራፊ የሀገራትን እጣ ፋንታ ሊወስን አይገባም” በሚል ስምምነት ጉባዔው መጠናቀቁንም ነው የገለፁት፡፡
በአፎሚያ ክበበው