Search

ከአሸዋማው የባህር ዳርቻ እስከ ኤምሬትስ - ያልተነገረው የሚኬል አርቴታ ጉዞ

ማክሰኞ ሐምሌ 07, 2018 137

ይህ ታሪክ የሚጀምረው በስፔኗ ሳን ሴባስቲያን የባህር ዳርቻ ላይ ነው። ሁለት ትንንሽ ልጆች በየቀኑ አሸዋው ላይ ኳስ እየተጫወቱ አደጉ። ሁለቱም አንድ ትልቅ ህልም ነበራቸው፤ አንድ ቀን ዓለም የሚያደንቃቸው ተጫዋቾች መሆን። ዛሬ ግን ዓለም የሚያከብራቸው ታላላቅ አሰልጣኞች ሆነዋል - ሚኬል አርቴታ እና ሻቪ አሎንሶ ናቸው።  

የዛሬ ባለ ታሪካችን ከሃያ ዓመታት በኋላ ታላቁን ክለብ አርሰናል የፕሪሚየር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ ያደረገው ጎልማሳው አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ነው። አርቴታ በልጅነቱ ጨዋታዎችን ከሌሎች በተለየ መልኩ ያነብ እንደነበር አሰልጣኞቹ ይመሰክራሉ። ይህ ጥልቅ እግር ኳሳዊ እውቀቱ ወደ ታዋቂው የባርሴሎና አካዳሚ ‘ላማሲያ’ ወሰደው።

ሜዳ ውስጥ እጅግ ቁም ነገረኛና ስሜታዊ፣ ከሜዳ ውጪ ግን ተጫዋች፣ ጥልቅ አስተሳሰብ ያለው እና በፈጠራ የተሞላ ስብዕና ነበረው። በባርሴሎና ዋናው ቡድን ውስጥ ቦታ ማግኘት ሲከብደው፣ በ19 ዓመቱ ወደ ፓሪስ ሴንት ዠርሜን አቀና። በወቅቱ ከዓለም ኮከቡ ሮናልዲንሆ ጋር ክፍል ከመጋራቱም በላይ፣ እንደ ጄይ ጄይ ኦኮቻ እና ኒኮላስ አኔልካ ካሉ ታላላቅ ተጫዋቾች ጋር ተሰለፈ።

አርቴታ ያንን የፓሪስ ቆይታውን "ወደ አንበሶች ዋሻ የተጣልኩ ያህል ነበር" ሲል ያስታውሰዋል። ከፒኤስጂ በኋላ በስኮትላንዱ ሬንጀርስ የአካል ጥንካሬን፣ በኤቨርተን ደግሞ የሊጉን አቅም ተምሮ፣ በ2011 በአርሰን ቬንገር ጥሪ አርሰናልን ተቀላቀለ። በአርሰናል ቤት ግብ አስቆጣሪ አልነበረም፤ ነገር ግን የመሀል ሜዳው ሞተር፣ ቡድኑን የሚያረጋጋ፣ ሁሉንም የሚያስተባብር መሪ ነበር።

አርሴን ቬንገርም የአምበልነት አርማውን ሲያስረክቡት የተመለከቱት ተጫዋችነቱን ብቻ አልነበረም፤ የወደፊቱን መሪነትም ጭምር ነበር። በዚህ ምክንያት ነው የቀድሞ የቡድን አጋሩ ሳንቲ ካዞርላ እንዲህ ሲል የመሰከረው። "ከአርቴታ ጋር ጨዋታ ማየት በጣም ያደክማል። ሁልጊዜ ቪዲዮውን ያቆማል፣ 30 ሰከንድ ወደ ኋላ ይመልሰውና 'ይህን አየኸው?' ይለኛል። እኔ ግን 'የማየው የቆመ ምስል ብቻ ነው!' እለው ነበር ይላል። "እርሱ ከተጫዋችነቱ በፊትም አሰልጣኝ ነበር" ብሎ ይመሰክራል።

አርቴታ በኢሚሬትስ ሁለት የኤፍ ኤ ካፕ ዋንጫዎችን በማንሳት ስኬታማ የተጫዋችነት ዘመኑን ሲያጠናቅቅ፣ ፔፕ ጋርዲዮላ የመሪነት ብቃቱን ተረድቶ ወዲያውኑ የማንቸስተር ሲቲ ረዳት አሰልጣኝ አደረገው። ከፔፕ ጎን ሆኖ ታክቲክን ብቻ ሳይሆን ክለብ እንዴት እንደሚመራ ተማረ። ሚኬል አርቴታ የአርሰናልን የአሰልጣኝነት መንበር ሲረከብ ክለቡ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ነበር።

ብዙዎች "ልምድ የለውም" ብለው ቢያጣጥሉትም፣ እርሱ ግን የማይደራደርባቸውን የስነ-ምግባር ህጎች በማውጣት የክለቡን ባህል ቀየረው። ዛሬ አርሰናልን ከመካከለኛ ደረጃ አንስቶ የፕሪሚየር ሊጉ ዋነኛ የዋንጫ ተፎካካሪ ከማድረግ ባለፈ ሻምፒዮን አድርጎታል፡፡ የአርቴታ ስልጠናዎች አስገራሚና ስነ-ልቦናዊ ትምህርት ያዘሉ ናቸው።

አንድ ቀን ተጫዋቾቹ እራት እየበሉ ሳለ፣ በድብቅ የኪስ አውላቂ ቀጥሮ ስልኮቻቸውን እና ቦርሳዎቻቸውን እንዲሰርቅ አደረገ። ተጫዋቾቹ ሲደናገጡ ንብረቶቻቸውን አውጥቶ፣ "በእግር ኳስም ሆነ በሌላ የህይወት ሁልጊዜ ንቁ መሆን አለባችሁ" በማለት ፈጽሞ ያልተጠበቀ ትምህርት ሰጥቷቸዋል። ሌላው መሳጭ ታሪኩ ደግሞ በ2021 ወደ ሊቨርፑል ከመጓዛቸው በፊት ያደረገው ነው።

አርሰናል ወደ ሊቨርፑል ተጉዞ መጫወት በስነ-ልቦና እጅግ ይከብደው ስለነበር፣ አርቴታ በልምምድ ሜዳ ላይ ግዙፍ ድምጽ ማጉያዎችን በማምጣት የሊቨርፑልን "You'll Never Walk Alone" መዝሙር በከፍተኛ ድምጽ ከፍቶ ተጫዋቾቹ በጫጫታው ውስጥ እንዲለማመዱ አድርጓል።  

ታላላቅ ስኬቶች የሚገነቡት በትንንሽ ዝርዝሮች ነው ብሎ ስለሚያምን፣ በኤሚሬትስ ስታዲየም የተጫዋቾች መውጫ መሸፈኛው እንዲነሳ በማድረግ የደጋፊው ድምፅ ተጫዋቾችን እንዲያነሳሳ አድርጓል። ፔፕ ጋርዲዮላ "እኔ ጋር እያለ ቀድሞኝ ውሳኔ የሚያሳልፍበት ጊዜ ነበር" ሲለው፤ አርሰን ቬንገር ደግሞ ገና ልምምድ ሜዳ ላይ እንዳዩት የወደፊት ታላቅ አሰልጣኝ እንደሚሆን እንደገመቱ ይናገራሉ።  

የአርቴታ ትልቁ ስኬት ያሸነፋቸው ዋንጫዎች ብቻ አይደሉም፤ በኤሚሬትስ ውስጥ የደበዘዘውን ተስፋ፣ እምነት እና የአሸናፊነት መንፈስ እንደገና መመለሱ ነው። እርሱ በእግር ኳስ ውስጥ ራዕይ፣ ትዕግሥት እና መሪነት ከተጣመሩ የት መድረስ እንደሚቻል የሚያሳይ ሕያው ምሳሌ ነው። የአርቴታ ጉዞ ገና አላበቃም...

በአዲስ የሺዋስ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: