በዚህ የክረምት ወቅት ልጆችዎ የት ይዋሉ ብለው ተጨንቀዋል? እንግዲያውስ አንድ ቦታ እንጠቁምዎ።
መንግሥት በአዲስ አበባ ከተማ ካከናወናቸው በርካታ የልማት ሥራዎች መካከል አንደኛው የፓርኮች ሥራ ሲሆን በወዳጅነት አደባባይ ቁጥር 2 ፓርክ ደግሞ ለልጆች መዝናኛነት ታስበው ከተሠሩት መካከል ይጠቀሳል።
የኢቢሲ ዶትስትሪም የወዳጅነት ቁጥር 2 ፓርክ በመገኘት ተቋሙ በውስጡ ምን ምን አገልግሎቶችን ይዟል ሲል ቅኝት አድርጓል።
ፓርኩ ለማኅበረሰቡ እጅግ ቀላል በሚባል ዋጋ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኝ ሲሆን በውስጡም በርካታ ቁጥር ያላቸው መጫወቻዎችን አካትቷል።
ፓርኩ ከልጆች እስከ ወጣቶች አገልግሎት የሚሰጡ የመጫወቻ ዓይነቶችን በውስጡ ያካተተ ሲሆን የእግር ኳስ ሜዳ፣ የቅርጫት ኳስ፣ ዥዋዥዌ፣ ባለ አራት እግር ሳይክሎች፣ መስፈንጠሪያ (ትራንፖል)፣ ልጆች የተለያዩ ነገሮችን የሚለማመዱባቸው ቻሌንጆች (ፈታኝ ጨዋታዎች)፣ ኒንጃ (የልጆችን አዕምሮ የሚያዳብሩ መሰናክሎች) እና የመሳሰሉት ይገኙበታል።
የልጆች መጽሐፍትን ሚያዘጋጁ ደራሲያን ከተቋሙ ጋር ለመሥራት ፕሮፖዛል በማስገባት የመጽሐፍ ይዘት ተገምግሞ ውል በመግባት ለልጆች ተደራሽ እንዲሆን እንደሚደረግ የተቋሙ ሱፐርቫይዘር አቶ ጫላ ነግረውናል።
ይህንን ክረምት አስመልክቶ በተቋሙ ልጆችን ታሳቢ ያደረጉ የተለያዩ የፈጠራ ችሎታቸውን የሚያዳብሩባቸው ልምምዶች ተዘጋጅተዋል።
እንደ ሥዕል መሣል፣ የሹራብ ሥራ፣ የሸክላ ሥራ፣ ምግብ ማብሰል እና የመሳሰሉት ተግባራትን የሚያከናውኑባቸው ዕድሎች ተመቻችተውላቸዋል።
ወላጆች ያለምንም ስጋት ልጆቻቸውን አምጥተው የሚያጫውቱበት ይህ ስፍራ ልጆች ደኅንነታቸውን የሚከታተል የተደራጀ አሠራር አለው።
ልጆች በድንገት ወድቀው ቢጎዱ እንኳ የመጀመሪያ ዕርዳታ የሚሰጥበት ክሊኒክ እዛው ጊቢ ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በሠለጠኑ ባለሙያዎች የታገዘ አገልግሎት ማግኘት ያስችላል።
ልጆች ከወላጆቻቸው ጋር ቢጠፋፉ ወላጅ እና ልጆች የሚገናኙበት ቺልድረን ሴንተር ክፍል በመኖሩ ስማቸውን በማይክራፎን በመናገር ወላጅ እና ልጅ እንዲገናኙ ይደረጋል።
ወላጆች ልጆቻቸው እየተጫወቱ አረፍ ማለት ቢፈልጉ የተለያዩ የምግብ እና መጠጥ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ባህላዊ እና ዘመናዊ ምግብ ቤቶች በመኖራቸው አገልግሎቱን ማግኘት ይችላሉ።
መንግሥት የማኅበረሰቡን አቅም ባገናዘበ እጅግ አነስተኛ ዋጋ በርካታ አገልግሎቶችን ልጆች እንዲያገኙ ዕድል ፈጥሯል።
በመሆኑም ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ተቋሙ ይዘው በመሔድ ጥሩ ጊዜ ማሳለፍ ይችላሉ።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ
#EBC #ebcdotstream #children #recreation #park #unitypark