ኢትዮጵያን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት፣ አዲስ አበባን ደግሞ የኢትዮጵያ የልማት ማሳያ ለማድረግ የተያዘው ውጥን አንዱ መስታወት ነው - የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት።
ከኮሪደር ልማቱ ጋር ተያይዞ ደግሞ የአዲስ አበባን ውበት አጉልቶ ያወጣው ዘመናዊ የመንገድ መብራት ይገኝበታል።
ሆኖም በመንገድ መብራቱ ፖሎች ላይ በግድየለሽነት በሚፈፀሙ ግጭቶች እና በስርቆት ምክንያት ጉዳት እየደረሰ መሆኑን በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ወንድሙ ሴታ ይናገራሉ።
በከተማዋ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ብቻ በዚህ የመንገድ መብራት ፖሎች ላይ በደረሰ ግጭት እና ስርቆት ምክንያት ከ16.5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ጉዳት መድረሱን ኢንጂነር ወንድሙ በተለይ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ሰዎች በቀን ብቻ ሳይሆን በማታም መሥራት እና የንግድ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚችሉባት ንቁ ከተማን መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን በማመን የከተማዋን የመንገድ ማብራት በተሻለ ሁኔታ እያስፋፋ ይገኛል።
በተለያየ ምክንያት የማይበሩ ከነበሩ 9 ሺህ 300 የመንገድ ማብራቶች መካከል 9 ሺህ 208 በመጠገን እና 909 አዳዲስ የመብራት ፖሎችን በመሥራት በኮሪደር ልማት ፕሮጀክት ከ3 ሺህ 400 በላይ አዳዲስ የመብራት ፖሎችን በመገንባት አገልግሎት እየሰጡ መሆኑን ኢንጂነር ወንድሙ ነግረውናል።
ይህም በከተማዋ ያለውን የመንገድ መብራት ፖሎችን ቁጥር ወደ 34 ሺህ 800 በማድረስ የመብራት ሽፋን በመጨመሩ ሰዎች ያለምንም ስጋት መንቀሳቀስ እንዲችሉ፣ የመንገድ ትራፊክ አደጋ እንዲቀንስ እና የምሽት የንግድ እንቅስቃሴ በተሻለ ሁኔታ እንዲካሄድ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።
ከዚህ በፊት “ከመጨለሙ በፊት ወደ ቤት ካልገባሁ ወንጀል ይፈፀምብኛል፤ ጉዳት ይደርስብኛል” የሚል ስጋት የነበረው የከተማዋ ነዋሪ አሁን ግን አምሽቶ መሥራት እና መንቀሳቀስ እንዲችል ዕድል ተፈጥሯል ብለዋል።
ሰዎች ምሽት ታክሲ ከመጠበቅ በእግር እንዲሄዱ እና ጤናቸውን እንዲጠብቁ የራሱን አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑንም አክለዋል።
በከተማዋ በዋና ዋና የመንገዶች አካባቢ የንግድ ተቋማት እና የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች እስከ ምሽቱ 4 ሰዓት ድረስ አገልግሎት እንዲሰጡ የከተማ አስተዳድሩ ግዴታ እንዲሆን መወሰኑን የተናገሩት ምክትል ከንቲባው፣ ይህ የተሳካ እንዲሆን የመንገድ መብራቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው ብለዋል።
ይሁን እንጂ በከተማዋ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የመንገድ መብራት መሠረት ልማቶች በግድየለሽ አሽከርካሪዎች በሚከሰት የመንገድ ትራፊክ አደጋ ፖሎች በግጭት እየወደቁ እና በስርቆት ምክንያት ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ጠቁመዋል።
ለአብነትም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በ71 ፖሎች ላይ ጉዳት በመድረሱ 16.5 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው ሀብት ላይ ውድመት ማስከተሉን ጠቁመዋል።
አብዛኛዎቹ ጉዳቶች በተሽከርካሪ የሚደርሱ ግጭጦች ቢሆንም የመብራት መሠረተ ልማት መቆጣጠሪያ ሳጥኖችን፣ ገመዶችን፣ ሽቦዎችን ቆርጠው እና ነቅሎ መውሰድ፤ በግንባታ ወቅት ለነባር መሠረተ ልማቶች አስፋላጊውን ጥንቃቄ አለማድረግ ሌሎች ተጠቃሽ መንሥኤዎች መሆናቸውን ገልጸዋል።
ለሕዝብ ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ የተገነቡ የመንገድ ዳር መብራት መሠረተ ልማቶች ላይ ጉዳት ያደረሱ አካላት በሕጉ መሠረት ወጪውን እንዲከፍሉ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
እስካሁንም በመብራት ፖሎች ላይ ግጭት ያደረሱ አሽከርካሪዎች 4.8 ሚሊዮን ብር በኢንሹራንስ እንዲከፍሉ ተደርጓል ብለዋል።
በስርቆት የተዘረፉ ከ800 ሺህ ብር በላይ የሚገመት ንብረት በፖሊስ ተይዞ በሕግ ተጠያቂነት ለማስፈን እየተሠራ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በመብራት መሠረት ልማቶች ላይ በግጭትም ሆነ በመስረቅ ያወደመ አካል የጠፋውን ንብረት መተካት ብቻ ሳይሆን በወንጀል ድርጊት ተጠያቂ ይሆናልም ብለዋል።
ነዋሪው ሁሉ በመሠረተ ልማቱ ላይ የሚደርስ ጉዳት በእኔ ሀብት ላይ የሚደርስ ጉዳት ነው የሚል እምነት መፍጠር፣ የመከላከል፣ የመጠበቅ እና አደጋ በሚደርስት ወቅት ለሚመለከተው አካል መረጃ መስጠት ኃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በላሉ ኢታላ
#EBC #ebcdotstream #AddisAbaba #Corridordevelopment