ዓለም ላይ በርካታ ደጋፊዎች ካሏቸው ክለቦች አንደኛው ነው፡፡ የተመሰረተው ደግሞ በ1886 ነው፡፡ የሰሜን ለንደኑን ክለብ ያክል በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ታሪክ ለአንድ ክፍለ ዘመን በተከታታይ የተሳተፈ ክለብ የለም፡፡
138ኛ ዓመቱ ላይ የሚገኘው አርሰናል ከምስረታው በኋላ ወደ ታችኛው የሊግ እርከን ወርዶ ዳግም ወደ እንግሊዝ ዋናው ሊግ ከተመለሰ በኋላ በተከታታይ ለ100ኛ ዓመት ጊዜ በመሳተፍ የሚስተካከለው አላገኝም፡፡
በእንግሊዝ ዋናው ሊግ በተሳለፈባቸው እነዚህ ዓመታት 4024 ጨዋታዎችን ሲያደርግ ከእነዚህ ውስጥ 1899 ጨዋታዎችን አሸንፏል፡፡
በ1023ቱ አቻ ሲለያይ በ1102 ጨዋታዎች ደግሞ ተሸንፏል፡፡ የሊጉን ክብር 13 ጊዜ ያነሳው አርሰናል በ100 ዓመታት የዋናው ሊግ ጉዞው የማሸነፍ ንጻሬው 47 በመቶ ሆኖ ተቀምጧል፡፡
በ100 ታሪካዊ ዓመታት ዴቪድ ኦሌሪ 558 የሊግ ጨዋታዎች በማድረግ ቀዳሚው ተጫዋች ሲሆን ቶኒ አዳምስ 504 ጨዋታዎች በማድረግ በአርሰናል መለያ በርካታ ጨዋታ ያደረገ 2ኛው ተጫዋች ነው፡፡
ፈረንሳዊው አጥቂ ቴየሪ ሄንሪ 175 ግቦች በማስቆጠር የክለቡ ታሪካዊ ኮከብ ነው፡፡ አርሰን ቬንገር በ22 ዓመታት የመድፈኞቹ ቤት የአሰልጣኝነት ቆይታቸው 828 ጨዋታዎች በማድረግ የሚስተካካላቸው የለም፡፡
በአርሰናል የ100 ዓመታት ተከታታይ የፕሪሚየር ሊግ ጉዞ ሌስተር ሲቲ 12 ጊዜ ወደ ታችኛው የሊግ ዕርከን በመውረድ ቀዳሚው ክለብ ሲሆን ሌሎች 6 ክለቦች 9 ጊዜ ወርደዋል፡፡
ኤቨርተን ከአርሰናል በመቀጠል ለ72 ተከታታይ ዓመታት በሊጉ በመሳተፍ የተቀመጠ ሲሆን ሊቨርፑል ለ64 ዓመታት በሊጉ በተከታታይ ተሳትፏል፡፡
በ1975 ከፕሪሚየር ሊጉ ወርዶ የነበረው ማንችስተር ዩናይትድ ለ51ኛ ተከታታይ ዓመት በሊጉ እየተሳተፈ
ይገኛል፡፡
ከ5 የአውሮፓ ታላለቅ ሊጎች ኢንተር ሚላን ለ116 ዓመታት በተከታታይ በመሳተፍ ቀዳሚው ሲሆን ባርሴሎና፣ ሪያል ማድሪድ እና አትሌቲክ ክለብ ከሊጉ ምስረታ ጀምሮ ወርደው የማያውቁ ክለቦች ናቸው፡፡
2003/2004 አንድም ጨዋታ ሳይሸነፍ የሊጉን ዋንጫ ያነሳው አርሰናል ለ100 ዓመታት በተከታታይ በመሳተፍም ከሌሎች ክለቦች በብዙ ርቀት ቆሟል፡፡
ትላንት በተጀመረው የ2025/26 የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ አርሰናል ከሜዳው ውጪ ከማንችስተር ዩናይትድ በሚያደርገው ጨዋታ 1900ኛ የሊግ ጨዋታውን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል፡፡
በአንተነህ ሲሳይ
#Arsenal #100times #PremierLeague