ከደንበኞቹ ዛሬ የቀረቡለትን የውጭ ምንዛሪ ማመልከቻዎች ሁሉንም በማጽደቅ የ420.4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ዋጋ ያላቸውን የተለያዩ የውጭ ምንዛሪ ዓይነቶች ለተለያዩ ፍላጎቶች መፍቀዱን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አስታወቀ።
ከሐምሌ 22 ቀን 2017 ዓ.ም ባንኩ ለ1 ሺህ 140 ደንበኞቹ በጥቅሉ የ541.4 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ዋጋ ያላቸውን የተለያዩ የውጭ ምንዛሪ ዓይነቶች መፍቀዱን ባንኩ ለኢቢሲ ዶትስትሪም በላከው መረጃ ገልጿል።
ይህም ከነዳጅ፣ ማዳበሪያ እና ሌሎች የአገልግሎት ክፍያዎች ጋር በተያያዘ በየቀኑ ከሚሰጠው መደበኛ የውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በተጨማሪ የተፈቀደ መሆኑን ነው የገለፀው።
እአአ ከጁላይ 1 ቀን 2025 ጀምሮ ለገቢ ንግድና ለአገልግሎት ክፍያ በአጠቃላይ 1.034 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ዋጋ ያለው የውጭ ምንዛሪ ክፍያ መፈፀሙን አክሎ ገልጿል።
በቀጣይም ከደንበኞች ፍላጎት እና ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ሀገራዊ ስትራቴጂያዊ ዘርፎች ጋር በማጣጣም ለውጭ ምንዛሪ አቅርቦት በመደበኛነት ምላሽ መስጠቱን እንደሚቀጥልም አረጋግጧል።
#ኢቢሲዶትስትሪም #የኢትዮጵያንግድባንክ #የውጭምንዛሪ