ባለፉት 4 ተከታታይ መክፈቻ ጨዋታዎች ላይ ግብ ያስቆጠረው ጊዮኬሬሽ ከ ፈጣኑ ሼሽኮ
ከሜዳ ላይ የተጫዋቾች የአልሸነፍ ባይነት ዕልህ እስከ ደጋፊዎች መበሻሸቅ እና አለፍ ሲል ለዳኞች ፈተና እስከ መሆን የደረሱ በርካታ አጋጣሚዎችን አሳልፈዋል።
በተለይ 1990ዎቹ መጨረሻ እና 2000ዎቹ መጀመሪያ የነበረው የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት ጨዋታው ከመካሄዱ 8 እና 15 ቀን በፊት ብዙ የሚባልለት ነው።
ኢትዮጵያን ጨምሮ ዓለም ላይ የበርካታ ደጋፊ ባለቤት የሆኑት ክለቦች ዛሬ ለ244ኛ ጊዜ ይገናኛሉ።
ማንቸስተር ዩናይትድ ከ አርሰናል
ከሰር አሌክስ ፈርጉሰን በኋላ መንገዱ የጠፋበት ማንቸስተር ዩናይትድ ረብጣ ገንዘብ አውጥቶ ስም ያላቸውን ከዋክብት ከማስፈረም ልምድ ያላቸውን አሠልጣኞች ጭምር ወደ አልድ ትራፎርድ ቢወስድም ስኬቱም አስፈሪነቱም ከስኮትላንዳዊው ሰው ጋር አብሮ ጠፍቷል።
በተለይ ያለፉት ጥቂት ዓመታት ጉዞው የቁልቁለት ሆኖበታል።
በተቃራኒው ከሊጉ ዋንጫ ጋር ከተገናኝ ከ20 ዓመት በላይ የሆነው አርሰናል የቀድሞ ተጫዋቹን አለቃ አድርጎ ከሾመ በኋላ ወደ ዋንጫ የሚወሰስደው ትክክለኛ መንገድ ላይ እንዳለ አሳይቷል።
የፔፕ ጋርዲዮላ ደቀ መዝሙር የሆነው ሚኬል አርቴታ ባለፉት 3 ተከታታይ ዓመታት ወደ ዋንጫው ተጠግቶ ያጠናቀቀባቸው ዓመታት ለዚህ ማሳያ ይሆናሉ።
ቀያይ ሰይጣናቱ ከ ከመድፈኞቹ በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመጀመሪያ ሳምንት ዛሬ በኦልድ ትራፎርድ የሚያደርጉት ጨዋታ እንደ ቀደሙት ጊዜያት ሁሉ ትልቅ ግምት አግኝቷል።
ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ መክፈቻ ሲገናኙ በታሪክ ይህ ለ6ኛ ጊዜ ሲሆን ሁለት ሁለት ጊዜ ተሸናንፈዋል አንዱን ደግሞ በአቻ ውጤት አጠናቀዋል።
ዩናይትድ የቱንም ያክል አስቸጋሪ ጊዜ ቢያሳልፍም በሜዳው ከአርሰናል በሚያርገው ጨዋታ በቀላሉ እጁን እንደማይሰጥ በተደጋጋሚ አሳይቷል።
በኦልድ ትራፎርድ ከአርሰናል ባደረጋቸው ያለፉት 18 ጨዋታዎች የተሸነፈው በሁለቱ ብቻ ሲሆን በ10 ጨዋታዎች ደግሞ አሸንፏል።
አርሰናል በሊጉ ከዩናይትድ በተገናኘባቸው ያለፉት 14 አጋጣሚዎች የበላይነቱን ይወስዳል። የተሸነፈው በሁለቱ ብቻ ሲሆን 8 ጊዜ አሸንፏል።
በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት 15ኛ ደረጃን ይዘው የጨረሱት ፖርቹጋላዊው አሠልጣኝ ሩብን አሞሪም ዩናይትድን ወደ ተፎካካሪነት ለመመለስ በዝውውር መስኮቱ በንቃት እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ቤንጃሚን ሼሽኮ፣ ማቲያስ ኩንሀ እና ብሪያን ምቤሞ የፊት መስመሩ መሪ ሆነው ቀያይ ሰይጣናቱ ቤት የደረሱ ናቸው።
በኦልድ ትራፎርዱ ፍልሚያ በአዳዲስ ከዋክብት የተገነባው የዩናይትድ የፊት መስመር ባለፉት ዓመታት እጅግ ጠንካራ ከሆነው የአርሰናል የተካላካይ ክፍል የሚያደርጉት ፍጥጫም የሚጠበቅ ይሆናል።
ስፔናዊው አሠልጣኝ ሚኬል አርቴታ በዋናነት የፊት መስመሩ ላይ ቪክቶር ጊዮኬሬሽን ሁነኛ አጥቂ አድርጎ ወደ ኢምሬትስ ማምጣቱ ምን አልባትም ለ3 ተከታታይ ዓመታት ያጣውን ዋንጫ ለማግኝት ዕድል እንደሚፈጥርለት በማመን ነው።
በዛሬው ጨዋታ በቋሚነት እንደሚጀመር የሚጠበቀው ስዊዲናዊው አጥቂ ባለፉት 4 ተከታታይ ዓመታት የሊጉ የመክፈቻ ጨዋታዎች ላይ ግብ አስቆጥሯል።
በሌላ በኩል የአማካይ ክፍል ላይ የማርቲን ዙቢሜንዲ እና ደክላን ራይስ ጥምረት የተዋጣለት መሆኑን ከአትሌቲክ ቢልባኦ በነበረው ጨዋታ አሳይተዋል።
ከጨዋታው በፊት አሠልጣን ሩብን አሞሪም በሰጡት ሐሳብ በአራት ሳምንት ውስጥ የሚቀየር ነገር ባይኖርም የተላለ ተዘጋጅተናል፤ በሂደት የምንፈልገው ነገር ላይ እንደርሳለን ብለዋል።
የተሳካ የቅድመ ውድድር ዝግጅት እንደነበራቸው የተናገረው የመድፈኞቹ አለቃ ሚኬል አርቴታ በሂደት የሚፈልጉትን ቡድን እንደገነቡ እና ጨዋታውንም ለማሸነፍ መዘጋጀታቸውን ገልጿል።
100ኛ ዓመት ተከታታይ የሊግ ተሳትፎ ላይ የሚገኝው አርሰናል በሊጉ መክፈቻ ተሸንፎ ዋንጫውን አንስቶ የማያውቅ ሲሆን አጀማመሩን ለማሳመር ከምንጊዜም ተቀናቃኙ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል።
በጨዋታው ግብ ጠባቂው አንድሬ ኦናና የመሰለፉ ነገር ያልተረጋገጠ ሲሆን፣ ኑሴር ማዝራዊ እና ሊሳንድሮ ማርቲኔዝም በጉዳት ቡድናቸውን የማያገለግሉ ተጫዋቾች ናቸው።
በአርሰናል በኩል ከሌአንድሮ ትሮሳረድ እና ገብርኤል ጀሱስ ወጪ አዲስ ጉዳት እንደሌለ ይፋ ሆኗል።
12 ሰዓት ከ30 ላይ የሚጀምረውን ተጠባቂ ጨዋታ ሲሞን ሁፐር በዋና ዳኝነት የሚመሩትም ይሆናል።
በአንተነህ ሲሳይ
#ebcsport #manchesterunited #arsenal #premierleague