Search

ለጣና ሐይቅ ደህንነት ወሳኝ የሆነው በሐይቁ ዳርቻ የሚገኙ ተቋማት ኃላፊነት

እሑድ ነሐሴ 11, 2017 104

የጣና ሐይቅን ደህንነት በዘላቂነት ለማስጠበቅ የሕግ ማዕቀፎችን ማስተግበር እንደሚገባ በአማራ ክልል በምክትል ርዕሠ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) አሳሠቡ።
 
የአማራ ክልል አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን በጣና ሐይቅ ደቡባዊ ክፍል ከሚገኘው የባህርዳር ከተማ ጣና ዙሪያ ሆቴሎች፣ ተቋማት እና የንግድ ድርጅቶች ጋር በሐይቁ ደህንነት ዙሪያ የሚመክር መድረክ አካሂዷል።
 
በወቅት በጣና ሐይቅ ዳርቻ የሚገኙ የንግድ ተቋማት እና ድርጅቶች የሐይቁን ደህንነት እና ለብዝሀ ሕይወት ሃብት ጥበቃው ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ተብሏል።
 
በመድረኩ ድረስ ሳህሉ (ዶ/ር) እንደገለፁት፤ የውሃ አካላት ጥበቃ እና ልማት ዘላቂ ሥራ ሆኖ እንደቀጠለ ይገኛል ብለዋል።
 
በርካታ የብዝሃ ሃብትን የያዘውን የጣና ሐይቅ ደህንነት በዘላቂነት ለማስጠበቅም በጉዳዩ ላይ የወጡ አዋጆችን እና ሌሎች የሕግ ማዕቀፎችን በተገቢው መንገድ ማስተግበር ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
 
የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊ አቶ ተስፋሁን አለምነህ በበኩላቸው፤ የጣናን ህልውና ለማስጠበቅ በየዓመቱ የመጤ አረም ማስወገድ፣ የባህሩ ውሃ ሲቀንስ ዳር ላይ የሚከናወን እርሻን መከላከል እና የውሃ አዘል መሬቶችን ዘላቂነት ማልማት ላይ በርካታ ስራዎች ስለመከናወናቸው አስገንዝበዋል።
 
በጣና ሐይቅ ላይ ሕይወታቸውን የመሠረቱ ተጠቃሚዎችን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠቃሚዎች በመሆናቸው ለሐይቁ ደህንነት ድርሻቸው የጎላ ነው ብለዋል።
 
በመድረኩ የውሃ አዘል መሬት ልማትና የአካባቢ ጥበቃ ዓለም አቀፍ መርሆች፣ የጣና ሐይቅ የደህንነት ችግሮች እና የተቋማቱ ሚናን አስመልክቶ መነሻ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።
 
 
በራሔል ፍሬው
 
አዳዲስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የኢቢሲን መተግበሪያ ከአፕ ስቶር እና ፕለይ ስቶር አውርደው ዲጂታል ኢቢሲን ይቀላቀሉ።
 
አንድሮይድ (Android) ስልክ የምትጠቀሙ በዚህ ሊንክ ➡️ https://shorturl.at/6KegY
 
አይኦኤስ (iOS) ስልክ የምትጠቀሙ ደግሞ በዚህ ሊንክ ➡️ https://shorturl.at/hFuA1