Search

የመድፈኞቹ 1900ኛ የፕሪሚየር ሊግ ድል እና የማንችስተር ዩናይትድ በሽንፈት ውስጥ የታየ ተስፋ

Aug 18, 2025

“ማጥቃት ላይ የተመሰረተ አጫዋዎት ጨዋታዎችን እንድታሸንፍ ያደርግሀል፡፡ መከላካል ግን ከዋንጫ ጋር ያገናኝሀል” የቀድሞው የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሰር አሌከስ ፈርጉሰን የተናገሩት ነው፡፡በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የመክፈቻ መርሀ ግብር ማንችስተር ዩናይትድ 75ሺ ተመልካቾች በታደሙበት ኦልድ ትራፎርድ በአርሰናል 1 ለ 0 ተሸንፏል፡፡ ምንም እንኳን ጨዋታው በትክክልም ውጤቱን የሚገልጽ ባይሆንም አመቱን በሽንፈት ጀምሯል፡፡ ኤሪክ ቴንሀን በመተካት ማንችስተር የደረሱት ወጣቱ አሰልጣኝ ሩብን አሞሪም ባለፉት ዓመታት ምህዋሩ የጠፋበትን ክለብ ወደ ቀደመ ጥንካሬው ለመመለስ የቡድን ግንባታውን ለመጀመር ፍንጭ የሰጡበትን ምሽት አሳልፈዋል፡፡
ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ በክረምቱ የተጫዋቾች የዝውውር መስኮት ያስፈረሟቸው የፊት መስመር ተጫዋቾች ከኳስ ጋርም ይሁን ያላ ኳስ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ለቀጣይ የቡድኑ ውጤት መመለስ ቁልፍ ተጫዋቾች እንደሚሆኑ ገና በመጀመርያው ጨዋታ አሳይተዋል፡፡
ማንችስተር ዩናይትድ በሜዳው ባደረገው ጨዋታ በሁሉም የጨዋታ መመዘኛዎች ከአርሰናል ተሸሎ አምሽቷል፡፡ በኳስ ቁጥጥሩም፣ የግብ ዕድሎችንም በመፍጠር፣ ኢላማቸውን የጠበቁ ሙካራዎችን በማድረግ ቀያይ ሰይጣናቱ ከመድፈኞቹ የተሸሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን በእግር ኳስ እነዚህ ሁሉ ጉዳዮች ወደ ሚጨበጥ ውጤት እስካልተቀየሩ ድረስ ዋጋ አይኖራቸውም፡፡ በኦልድ ትራፎርድ የሆነም ይሄው ነው፡፡
በጨዋታው ባለሜዳዎቹ የተሸሉ ቢሆኑም አሁንም ማስተካካል ያለባቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ በዋናነት የጎደለውን ሚዛን ማስተካከል ይሆናል፡፡ የዩናይትድ የፊት መስመር ብዙ ተስፋ የሚጣልበት ቢሆንም አማካይ እና ተከላካይ ክፍሉ ግን የሚቀሩት በርካታ ስራዎች ይኖራሉ፡፡
 
ባለፈው አመት 10 የግብ ዕዳ ይዞ ያጠናቀቀው ክለቡ የመከላከል ችግር እንደነበረበት የሚያሳይ ሲሆን አሰልጣኙ ከግብ ጠባቂ ጀምሮ ቀዳዳዎችን መሙላት ካልቻሉ በዚህ አመት የአምናው ስላለመደገሙ ዋስትና አይኖርም፡፡ በአንድ ቡሩኖ ፈርናንዴዝ ላይ ጥገኛ የሆነው የአማካይ ክፍሉም ቢሆን ሌላ ሁነኛ ተጫዋች የሚፈልግ ነው፡፡
በሌላ በኩል ቀያይ ሰይጣናቱ የቆመ ኳሶችን መከላከል ላይ ከሁሉም የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ ከ2023/24 የውድድር ዓመት በኋላ የዩናይትድን ያክል የማዕዘን ግብ የተቆጠረበት ክለብ የለም፡፡ ትላንት ምሽት ካላፊዮሪ ያስቆጠራትን ጨምሮ 23 ግቦች ተቆጥረውበታል፡፡
የ40 አመቱ አሰልጣኝ ሩብን አሞሪም ዩናትድን ከተረከቡ በኋላ ካደረጓቸው 28 የሊግ ጨዋታዎች ያሸነፉት ሰባቱን ብቻ ሲሆን በ16ቱ ደግሞ ተሸንፈዋል፡፡ የዩናይትድን የጨዋታ ሚዛን ማስተካለል እና እንደ ተጋጣሚ ሆኖ ለመቅረብ መስራት እዲሁም ለኋለኛውን ክፍል መፍትሄ ማበጀት የአሰልጣኙ ትልቅ የቤት ስራም ይሆናል፡፡
ባለፉት ሦስት ተከታታ ዓመታት 2ኛ ሆኖ ከማጠናቀቅ ያለፈ ትልቁን የሊግ ክብር ማሳካት ያቻለው አርሰናል ምንም እንኳን በተጋጣሚው ብዙ ብልጫ ቢወሰድበትም ወሳኙን ሦስት ነጥብ በማሳካት ጅማሮውን አሳምሯል፡፡ በአርሰናል የተጫዋችነት ዘመኑ በሊጉ ወደ ኦልድ ትራፎርድ አምርቶ አንደም ጨዋታ አሸንፎ የማያውቀው ሚካኤል አርቴታ በአሰልጣኝነት ግን ለ2ኛ ጊዜም ዩናይትድን በሜዳው እና ደጋፊው ፊት ያሸነፈበትን ውጤት አስመዝግቧል።
 
ነገር ግን ከሊጉ ዋንጫ ጋር ከተገናኘ ሁለት አስርት ዓመታትን ላስቆጠረው የሰሜን ለንደኑ ክለብ ይሄ በቂ አይደል፡፡ በተለይ ባለፉት 3 እና 4 ዓመታት የቡድን ግንባታ ላይ ያሳለፈው አሰልጣኝ ሚካኤል አርቴታ የተሰጠውን በቂ ጊዜ ለመጠቀም የአርሰናልን የዋንጫ ረሀብ ማስታገስ የሚጠበቅበት ይመስላል፡፡
አርሰናል በሊጉ መክፈቻ ከሜዳው ውጭ ለዚያውም ከምንጊዜም ተቀናቃኙ ማንችስተር ዩናይትድ ሦስት ነጥብ ማግኘቱ እንደ አንድ ጥንካሬ የሚወሰድ ነው፡፡ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ የቀድሞው የሊቨርፑል አማካይ ስቴቨን ጀራርድ በሰጠው ሃሳብ አርሰናል ጥሩ ባልሆነበት ምሽት ዩናይትድን በሜዳው ማሸነፍ መቻሉ ረጅም ርቀት እንደሚጓዝ ማሳያ ነው ብሏል፡፡
በዝውውሩ በሁሉም የጨዋታ ክፍል በንቃት ተሳትፎ ያደረገው አርሰናል ከግብ ጠባቂው ዴቪድ ራያ ጀምሮ የኋላ መስመሩ ጥንካሬ አሁንም አብሮት እንዳለ በሚገባ አሳይቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ የትላንቱን ጨዋታ ብቻ መመልከት በቂ ይሆናል፡፡ ለዚህም ይመስላል የቀድሞው የዩናትድ አንጋፋው አሰልጣኝ ሰር አሌከስ ፈርጉሰን ጠንካራ ተከላካይ ስላለው ቡድን ሲናገሩ መካላከል ከዋንጫ ጋር ያገናኛል የሚል ሃሳባቸውን የሰጡት፡፡
ባለፉት ሦስት የውድድር ዓመታት በሊጉ ዝቅተኛ ግብ ከተቆጠረባቸው ክለቦች ቀዳሚው አርሰናል የቆሙ ኳሶችን በመጠቀም የሚስተካከለው አልተገኘም፡፡ የቆሙ ኳሶች አሰልጣኙ ኒኮላስ ጆቨርን ከማንችስተር ሲቲ ካመጣ በኋላ የእንግሊዝ ክቦች ፈተና ሆኗል፡፡ ከ2021/22 የውድድር ጊዜ ጀምሮ 71 የቆሙ ኳሶችን ከመረብ አሳርፏል፡፡
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ በተከታታይ በመሳተፍ 100ኛ ዓመታቸው ላይ የሚገኙት መድፈኞቹ በአንድ ክፍለ ዘመን ጉዟቸው 1900ኛ ድላቸውን አሳክተዋል፡፡ መድፈኞቹ ምንም እንኳን ከቴአትር ኦፍ ድሪምስ ሦስት ነጥብ ቢያገኙም በቀጣይ ሊያስተካክሏቸው የሚገቡ ጉዳዮችስ የትኞቹ ይሆናሉ?
ባለፉት ዓመታት ጥያቄ የሚነሳበት እና አሁንም መሻሻል ያልቻለው ማርቲኔሊን የሚካኤል አርቴት ያልተቀረፈ ችግር ሆኗል፡፡ ብራዚላዊው የመስመር ተጫዋች ሲከላከል ጥሩ ቢሆንም በቦታው ግን ግብ ማስቆጠርም ይሁን ለግብ የሚሆኑ ኳሶች ላይ በመሳተፍ የሚጠበቅበትን ማደረግ አለመቻሉ የአርሰናልን ቡድን ጎደሎ እንዲሆን የሚያደርገው ነው፡፡
ሌላኛው ደግሞ በ64 ሚሊዮን ፓውንድ ኢምሬትስ የደረሰውን ቪክቶር ጊዮኬሩሽን ወደ ጨዋታ ማስገባት ይሆናል፡፡ ብዙ ለሚጠበቅበት የ27 ዓመቱ አጥቂ ከጀርባው የሚገኙ እንደ ኦዴጋርድ አይነት የፈጠራ አቅማቸው ክፍ ያሉ ተጫዋቾች የግብ ዕድሎችን እንዲፈጥሩ ነጻነቱን መስጥት አስፋለጊ ይሆናል፡፡
በደክለን ራይስ፣ ማርቲን ዙቢሜንዲ እና ማርቲን ኦዴጋርድ የሚመራውን የአማካይ ክፍል የኳስ ቁጥጥሩ ላይ ይበልጥ እንዲሰራ ተለዋዋጭ በመሆን ለአጥቂዎች አደጋ የሚፈጥሩ ኳሶችን እንዲያቀብል ማድረግ የስፔናዊው ታክቲሺያን ቀሪ የቤት ስራዎች ይሆናሉ፡፡
በአንተነህ ሲሳይ