የክረምት ወቅት በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቻችን ላይ ቅዝቀዘዜ በደንብ የሚሰማበት ወቅት ነው፡፡
በመሆኑም በዚህ የክረምት ወቅት የጥርስ ሕመም ስሜት ጎልቶ የሚሰማበት መሆኑ በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡
ኢቢሲ በአዲሰ ቀን መሰናዶው ክረምት እና የጥርስ ሕመም ምን ያገናኛቸዋል ሲል ከባለሙያ ጋር ቆይታ አድርጓል፡፡
በሕክምናው ዘርፍ 14 ዓመታት ያገለገሉት የጥርስ እና የአፍ ውስጥ ሕክምና ባለሙያው ተድላ ተሰማ፤ ክረምት እና የጥርስ ሕመም ሰፊ ግንኙነት እንዳላቸው አንስተዋል፡፡
ዶ/ር ተድላ የጥርስ ሕመም ችግሮች እንደ ጥርስ መቦርቦር፣ የድድ መሸሽ፣ የጥርስ መበላት እና የመሳሰሉት በበጋ ወቅት ሙቀት በመሆኑ ሕመሙ ሳይሰማ ቆይቶ በክረምት ወቅት ሕመሙ እንደሚጎላ አብራርተዋል፡፡
ችግሩ ከ20 እስከ 50 የእድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ጎልቶ የሚታይ ቢሆንም፤ ጣፋጭ ነገሮችን በሚጠቀሙ ልጆች ላይም እየተስተዋለ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
የልጆች ጥርስ እንደ አዋቂዎች ጠንካራ ባለመሆኑ ለመጎዳት ቅርብ መሆኑንም ነው ዶ/ር ተድላ አያይዘው የገለጹት፡፡
ለጥርስ ሕመም መከሰት ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የጥርስ ፅዳትን አለመጠበቅ መሆኑን ጠቅሰው፤የማህበረሰቡ የአፍ እና የጥርስ ጤናን የመጠበቅ ባሕል ዝቅተኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ጥርስን ከመታጠብ ጋር በተያያዘ የጥርስ መስታወት ይጎዳል የሚለው አመለካከት የተሳሳተ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
ጥርስ በሚታጠብበት ወቅት በርካታ ቆሻሻዎች ድድ ውስጥ ተቀምጠው ስለሚገኙ ከጥርሱ ላይ በሚወገዱበት ወቅት የቅዝቃዜው ስሜት ሕመም ይፈጥራልም ነው ያሉት፡፡
የጥርስ ሕመም ከሌሎች የሕመም አይነቶች ከፍ ያለ መሆኑን ገልጸው፤ ይህም የሆነበት ምክንያት በአንዲት ዘለላ ጥርስ ውስጥ የደም ስሮች እና የነርቭ ክፍሎች በመገኘታቸው ነው ብለዋል፡፡
ጥርስ ችግር በሚኖርበት ወቅት የደም ስር ስለሚሰፋ የነርቭን ክፍል አጣብቆ በመያዝ ከፍተኛ ሕመም እንዲፈጠር ምክንት ይሆናል ነው ያሉት ባለሙያው፡፡
የጥርስ ሕመምን ለመከላከል ጣፋጭ ምግቦችን እና መጠጦችን መቀነስ፣ ሲጋራ አለማጨስ እንዲሁም በየቀኑ የአፍ ንጽሕናን መጠበቅ እንደሚያስፈልግ የጤና ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡
በንፍታሌም እንግዳወርቅ