Search

የቡሄ (የደብረ ታቦር) አከባበር

Aug 18, 2025

ኢትዮጵያ የበርካታ የማይዳሰሱ ባህላዊ ቅርሶች ባለቤት ናት። ከእነዚህ መካከል ደግሞ ሐይማኖታዊ ትውፊት ያላቸው በዓላት ይጠቀሳሉ።

በነሐሴ ወር ከሚዘወተሩ ባህላዊ እና ሐይማኖታዊ በዓላት አንዱ ደግሞ ቡሄ ነው።

የቡሄ (የደብረታቦር) በዓል ነሐሴ 13 ቀን በየዓመቱ ይከበራል።

የቡሄ (የደብረታቦር) በዓል መነሻው ሐይማኖታዊ መሰረት መሆኑን የአዲስ አበባ ባህል እና ኪነ-ጥበብ ቢሮ ከፍተኛ የቅርስ ጥናት ተመራማሪ  መምህር መክበብ ገ/ማሪያም ለኢቢሲ ዶት ስትሪም ተናግረዋል፡፡

ነሐሴ 13 ቀን በሐይማኖታዊ አስተምህሮው ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት ነው ተብሎ ስለሚታሰብ የደብረ ታቦር በዓል እንደሚከበርም ያወሳሉ።

ይህ በዓል ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ ይዘት እንዳለውም ያነሳሉ። ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን በገለጠበት ወቅት የነበረውን ብርሃን ለማስታወስም ችቦ እንደሚበራም ነው የሚያስረዱት፡፡

"ደብር" ተራራ "ታቦር" ኢየሱስ ክርስቶስ የተገለጠበት ቦታ ሲሆን፣ ቃላቱ ተጣምረው "ደብር-ታቦር" ወይም "የታቦር ተራራ" የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል ይላሉ። ፡

በነጎድጓዳማ ድምጽ ብርሃነ መለኮቱን መገለጡን ለማስታወስም  ልጆች፣ ወጣቶች ጅራፍ እንደሚያጮሁም ነው መምህር መክብብ ያነሱት።

ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ተራራ ብርሃነ መለኮቱን ሲገልጽ በአካባቢው የነበሩ እረኞች ይሄን ተዓምር ለማየት ወደ ተራራው ሄደው ነበር::

እረኞች በኢየሱስ ክርስቶስ ሚስጥር ተገርመው በተራራው እጅግ በመቆየታቸው ቤተሰቦቻቸው ዳቦ ይዘው፣ ችቦ ለኩሰው ልጆቻቸውን ፍለጋ መሄዳቸውነ ለማስታወስም ሙልሙል ዳቦ እንደሚዘጋጅ ነው ታሪኩን ያስረዱት።

አሁን ድረስ በቡሄ “ሆዬ ሆዬ” እያሉ ለሚመጡ ሕጻናት እና ታዳጊዎች ዘምረው እንዳበቁ የሚሰጠው “ሙልሙል” ዳቦም ከዚሁ ታሪክ ጋር የሚያያዝ ነው ሲሉ አንስተዋል።

ሕፃናቱም በመዝሙር “ውለዱ ክበዱ፣ ሀብት አግኙ ” ብለው መርቀዉ እና አመስግነው ይመለሳሉ፡፡

ወቅቱ የክረምት ጨለማ አልፎ ብርሃን የሚወጣበት፤ ሰማይ ከጭጋጋማነት ወደ ብሩህነት የሚለወጥበት መሸጋገሪያ እንደሆነም ይታመናል ይላሉ።

ይህ ሐይማኖታዊ እና ባህላዊ የማይዳሰስ ቅርስ ሳይበረዝ ለትውልዱ መተላለፍ እንደሚገባውም መምህር መክብብ ገልጸዋል፡፡

 

በሜሮን ንብረት