እዚህ ቤቶች እንደምን ናችሁ፣
በዓመት አንድ ቀን መጣንላችሁ …
በወርሐ ነሐሴ ከወሩም በአሥራሶስተኛው ቀን የቡሄ (ደብረታቦር) በዓል መዳረሻ ላይ የምንሰማው በጭፈራ የታጀበ የልጆች ዜማ ነው፡፡
ልጆች ቆርኪ ቀጥቅጠው ከሚይዙት ዱላ ጋር አያይዘው መሬቱን በመደብደብ እያንከሻከሹ የቤቱን አባወራ እና እማወራ ስም እያነሱ በማሞገስ ያዜማሉ፡፡
በምላሹ እንደቀድሞው ባሕል ልጆች ሙልሙል ዳቦ የሚሰጣቸው ሲሆን አሁን አሁን ገንዘብ መስጠት እየተለመደ መጥቷል፡፡
መነሻው ሐይማኖታዊ መሰረት የሆነው የቡሔ (ደብረታቦር) በዓል፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በድምቀት ይከበራል፡፡
የአከባበር ሥነ-ሥርዓቱ ከቦታ ቦታ በጥቂቱ ቢለያይም ጅራፍ ማጮህ እና ችቦ ማብራት በብዙዎች ዘንድ የተለመደ ነው፡፡
ልጆች ከቃጫና ከልጥ ተገምዶ የተሰራውን ጅራፋቸውን በማጮህም የዓሉን መድረስ ያበስራሉ፡፡
በቡሄ በዓል በሚደረገው የሆያ ሆዬ ጭፈራ በርካታ ሥነ-ቃላዊ ግጥሞች ይስተናገዳሉ፡፡
ቀደም ባለው ጊዜ እና ባሁኑ ዘመን የሚሰሙት የሆያ ሆዬ የሥ-ነቃል ግጥሞች ይለያያሉ፡፡
ሥነ-ቃል በባህሪው ተለዋዋጭ ነው፤ ተለዋዋጭነቱም በቦታ፣ ሁኔታ እና በጊዜ (መቼቱ እና ጭብጡ )ከዘመናት ጋር የነበራቸው ቆይታን ያማከለ ሆኖ እንደአስፈላጊነቱ የሚቀያየርበት ሁኔታ ይኖራል፡፡
ይህ ቢሆንም የዘመናችን የሆያ ሆዬ ጨፋሪዎች የሚያወጧቸው ሥነ-ቃላዊ ግጥሞች ኢትዮጵያዊነትን የማያንፀባርቁ መሆናቸው በብዙዎች ዘንድ ይነሳል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ከኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ጋር ቆይታ ያደረጉት መጋቢ ሐዲስ ሮዳስ ታደሰን ትዝብታቸውን አጋርተውናል፡፡
በደብረታቦር በዓል ልጆች ባለማወቅ ወይም በትክክል የሚመራቸው ሰው በማጣት መልካም ያልሆኑ እና ምንም ትርጉም የማይሰጡ ግጥሞችን በማውጣት እንደሚጨፍሩ ገልፀዋል ፡፡
ይህንን ለማስተካል ኃላፊነቱን ቤተክርስቲያን እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት መውሰድ እንደሚገባቸው ነው መጋቢ ሐዲስ ሮዳስ የሚያነሱት፡፡
የጥንቱን ግጥም ማስጠናት እንዲሁም ልጆችን በመምራት ወደ ትክክለኛው መንገድ ማምጣት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
ወጣቱ ትውልድ ባህል እና እሴቱን ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅበትም ገልጸዋል፡፡
ለዚህ ደግሞ ኃላፊነቱ የሁሉም በመሆኑ፣ የተሳሳቱ ግጥሞች እና አካሄዶች ሲስተዋሉ መምከር እና ማስተካከል ከሁሉም ማህበረሰብ የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል፡፡
በሐይማኖታዊ አስተምህሮው ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት ነው ተብሎ ስለሚታመን የደብረ ታቦር በዓል እንደሚከበር አንስተዋል።
በንፍታሌም እንግዳወርቅ