Search

በሲሪላንካ 3.1 ኪሎ ግራም የሚመዝን የሽንት ፊኛ ጠጠር በቀዶ ሕክምና ተወገደ

ረቡዕ ነሐሴ 13, 2018 141

በሲሪላንካ የሚገኙ የጦር ሠራዊት የሕክምና ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ የሕክምና ታሪክ ያስመዘገበ አስገራሚ ቀዶ ሕክምና አከናውነዋል።

ሐኪሞቹ ዕድሜያቸው 62 ዓመት የሆኑ ጡረታ የወጡ ወታደር የሽንት ፊኛ ውስጥ 3.1 ኪሎ ግራም የሚመዝን እና 13.37 ሴንቲሜትር ርዝመት ያለው የሽንት ፊኛ ውስጥ የነበረ ድንጋይ በስኬት ማስወገድ ችለዋል።

በኮሎምቦ የጦር ሠራዊት ሆስፒታል የተካሄደው ይህ ቀዶ ሕክምና በአውሮፓውያኑ 2008 በሕንድ ተመዝግቦ የነበረውን 1.1 ኪሎ ግራም የሽንት ፊኛ ጠጠር በመብለጡ፣ ጊነስ የዓለም ድንቃድንቅ ክብረ ወሰን መዝገብ በዓለም ላይ በክብደቱም ሆነ በትልቅነቱ የመጀመሪያው እንደሆነ መዝግቦታል።

ይህ ያልተለመደ የጤና ሁኔታ በሕክምናው ዓለም ትልቅ ትኩረት ያገኘ ሲሆን፣ ሕሙማንም ሆኑ ኅብረተሰቡ ስለ ሽንት ፊኛ ጠጠር አፈጣጠር በቂ ግንዛቤ እንዲኖራቸው የሚያደርግ ነው።

የሽንት ፊኛ ጠጠር የሚፈጠረው በሽንት ፊኛ ውስጥ ያለው ሽንት በሙሉ ወደ ውጭ ሳይወጣ ተከማችቶ በሚቀርበት ጊዜ፣ በሽንት ውስጥ የሚገኙ ማዕድናት እርስ በርስ በመያያዝ እና በመጠናከር ሒደት ነው።

ለዚህ ደግሞ የሽንት ፊኛ እብጠት፣ የፕሮስቴት ዕጢ ማበጥ ወይም መጨመር እንዲሁም ለሽንት መውጣት አስፈላጊ የሆኑ የነርቭ ችግሮች ዋና ዋና ምክንያቶች እንደሆኑ የሕክምና መረጃዎች ያመለክታሉ።

ይህንን ጠጠር ለማስወገድ የተደረገው የቀዶ ሕክምና ሙሉ በሙሉ የተሳካ የነበረ ሲሆን፣ ታካሚውም በአሁኑ ወቅት በጥሩ የጤና ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ እና በማገገም ላይ እንዳሉ ተገልጿል።

ይህ ክስተት ማንኛውም የሽንት ማጠናቀቅ ችግር ወይም የሽንት መዘጋት ምልክት ሲያጋጥም ፈጥኖ ወደ ሕክምና ተቋም በመሄድ ተገቢውን ምርመራ ማድረግ እና የጤና ክትትል ማድረግ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል።

በሲሳይ መንግሥቱ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: