Search

የቻይና ሮቦቶች ዩሴን ቦልትን የ100 ሜትር የዓለም ሪከርድ ሰበሩ

እሑድ ነሐሴ 17, 2018 62

በቻይና ቤጂንግ በተካሄደው በዓለም የሰው መሰል ሮቦቶች ውድድር ላይ የቻይና የቴክኖሎጂ ፈጠራ አዲስ የዓለም ታሪክ አስመዝግቧል።

በቤጂንግ ሰው ሰራሽ ሮቦት ፈጠራ ማዕከል የተገነባው ቲያንጎንግ አልትራ የተሰኘው ሮቦት 100 ሜትር ርቀቱን 9.39 ሰኮንድ በማጠናቀቅ የውድድሩ አሸናፊ ሆኗል።

ይህም በታዋቂው ጃማይካዊ የአጭር ርቀት ንጉስ አትሌት ዩሴን ቦልት የተያዘውን 9.58 ሰኮንድ የወንዶች የዓለም ክብረወሰን 19 ማይክሮ ሰኮንድ ነው ያሻሻለው።

በውድድሩ ሁለተኛ ደረጃን የያዘው ሃኖርስ ፍላይንት የተሰኘው ሮቦት በበኩሉ፣ ርቀቱን 9.47 ሰኮንድ በመጨረስ የቦልትን ሪከርድ ማሻሻል ችሏል።

በተጨማሪም ቅዳሜ ዕለት ቀደም ብሎ በተደረገ ሙከራ ላይ 100 ሜትሩን 9.32 ሰኮንድ በመሮጥ በሰኮንድ እስከ 14.5 ሜትር የሚደርስ አስደናቂ ፍጥነት ማስመዝገቡ ተገልጿል።

ይህም ባለፈው ዓመት ቲያንጎንግ አልትራ ውድድሩን 21.50 ሰኮንድ ካጠናቀቀበት ጋር ሲነጻጸር በቴክኖሎጂው ዘርፍ ምን ያህል ፈጣን እድገት እየመጣ እንደሆነ ያሳያል።

በዘንድሮው የቤጂንግ ብሔራዊ የፍጥነት ስኬቲንግ ኦቫል ውድድር ላይ 6 አህጉራት ከሚገኙ 16 ሀገራት የተወጣጡ 2 ሺህ 56 ሮቦቶች 51 የተለያዩ ዘርፎች ማለትም በሩጫ፣ በግማሽ ማራቶን፣ በእግር ኳስ፣ በጭፈራ እና በኢንዱስትሪ ተግባራት ተሳትፈዋል።

ቻይና ሰው ሰራሽ ሮቦቶችን እንደ ዋና ስትራቴጂካዊ የቴክኖሎጂ ዘርፍ በመውሰድ በማኑፋክቸሪንግ፣ በሎጂስቲክስ እና በዕለት ተዕለት የሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ያላቸውን ሚና ለማስፋፋት በከፍተኛ ሁኔታ እየሰራች ትገኛለች።

ትናንት የተጀመረው 2ኛው ዓለም የሰው መሰል ሮቦቶች ውድድር (World Humanoid Robot Games) የፊታችን ረቡዕ ይጠናቀቃል፡፡

በኢንቲሃድ አብራር

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: