Search

ለሌሎች ብርሃን ሰጥተው ያለፉት አንጋፋው አርቲስት

ረቡዕ ነሐሴ 14, 2017 148

አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ በሕይወት እያሉ የዓይን ብሌናቸው ብርሃን ላጡ ወገናኖቻቸው ብርሃን እንዲሆን ለመለገስ ቃል ገብተው ነበር፡፡

አንጋፋው አርቲስት ከኪነ-ጥበብ ሥራዎቻቸው ባለፈ የበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሳተፉ የሚታወቁ መልካም ስብዕና ያላቸው ልበ ቀና ሰው ነበሩ።

አንጋፋ አርቲስቶች፣ ተማሪዎቹ፣ አድናቂዎቹ እንዲሁም ወዳጅ ዘመዶቹ በተገኙበት በሸራተን አዲስ በተካሄደ የልደት ሥነ-ሥርት ላይ አንጋፋው አርቲስት ደበበ ሕይወታቸው ሲያልፍ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል ገብተው ነበር።

በዚህም በቃላቸው መሠረት የአንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ የዓይን ብሌን ለኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ገቢ ተደርጓል፡፡

በአርቲስቱ የትዳር አጋር  እና ቤተሰቦች መልካም ፍቃድ የዓይን ብሌኑ ለኢትዮጵያ ደም እና ህብረ ህዋስ ባንክ አገልግሎት ገቢ መደረጉን የተቋሙ የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ተወካይ ነጋ ደምሴ ለኢቲቪ ተናግረዋል።

አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ በሕይወት እያሉ ብዙ ሰዎች የዓይን ብሌናቸውን እንዲለግሱ ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በመስራት በርካታ አርቲስቶችን ቃል እንዲገቡ ማስቻላቸውንም ገልጸዋል።

አንጋፋው አርቲስት ደበበ እሸቱ በቃላቸው መሰረት የዓይን ብሌናቸውን ለግሰው ማለፋቸው ለሌሎች አርዓያ የሚሆን በሕይወት እያሉ ለህዝብ ያላቸውን ክብር ያሳዩበት ተግባር ነው ብለዋል አቶ ነጋ ደምሴ።

አክለውም በህዝቡ ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው ግለሰቦች በእንደዚ አይነት የሰብዓዊነት ሥራ ላይ መሳተፋቸው እና ተግባራዊ ማድረጋቸው ማህበረሰቡ  ግንዛቤ ለመፍጠር ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

እስካሁን 17 ሺህ ኢትዮጵያውያን ከህልፈታቸው በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል የገቡ ሲሆን፣ ከ300 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ደግሞ የዓይን ብሌን ልገሳ እንዲደረግላቸው እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡

በሔለን ተስፋዬ