Search

“ሕይወቴን ለማትረፍ የምጠብቀው የኢትዮጵያን ሕዝብ ነው” - ሳዳት ጀማል

ቅዳሜ ነሐሴ 17, 2017 53

ሳዳት ጀማል የቀድሞው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ብሔራዊ ቡድን ግብ ጠባቂ ነው፡፡

በተለያዩ መድረኮች ሀገሩን ወክሎ ተጫውቷል፡፡

ኢትዮጵያ ቡና፣ መከላከያ፣ ሙገር  እና ሐዋሳ ከነማ፣ ደብረ ብርሃን ብርድ ልብስ፣ አዲስ አበባ ፖሊስ እና  ኒያላ ተጫውቶ ያሳለፈባቸው ክለቦች ናቸው፡፡

በተጫዋችነት ዘመኑም ከተለያዩ ክለቦች  የጥሎ ማለፍ፣ የሲቲ ካፕ እና የሴካፋ ዋንጫዎችን አሸንፏል፡፡

ሳዳት ጀማል እግር ኳስ ካቆመ በኋላ ፊቱን ወደ አሰልጣኝነት አዙሮ እያገለገለም ነበር፡፡

በዋናነት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎች) የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ በመሆን ሰርቷል፡፡

ከልጅነቱ ጀምሮ በእግር ኳስ ያሳለፈው እና ከክለብ እስከ ብሔራዊ ቡድን የተጫወተው ሳዳት ጀማል አሁን በጠና ታሟል፡፡

ከእግር ኳስ ውጪ ሕይወት እንደሌለው የሚናገረው አሰልጣኝ ሰዳት ጀማል በከፍተኛ የጉበት ህመም እየተሰቃየ ይገኛል።

በገጠመው የጤና እክል በቅዱስ ጳውሎስ ሆስታል ህክምናውን ሲከታትል ቆይቷል ሳዳት። ይሁንና የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ቦርድ አባላት ህክምናውን በሀገር ውስጥ መቀጠል የማይቻል በመሆኑ ወደ ውጭ ሀገር ሄዶ እንዲታከም ውሳኔ አሳልፈዋል፡፡ 

በህንድ ህክምና እስከሚያገኝ ድረስ አቅሙን ከፍ ለማድረግ እና ሌሎች ተጓደኝ በሽታዎች እንዳይከሰቱ በአሚን አጠቃላይ ሆስፒታል ክትትል እየተደረገለትም ይገኛል፡፡

"ለተሻለ ህክምና ወደ ህንድ ለመሄድ የሚበቃ ገንዘብ የለኝም፤ የምጠብቀው የኢትዮጵያን ሕዝብ ነው" ያለው የቀድሞው የብሔራዊ ቡድኑ የግብ ዘብ ህዝቡ እንዲያሳክመው  ጥያቄውን አቅርቧል።

ከታመምኩበት ጊዜ ጀምሮ ሕዝቡ ላሳየኝ ፍቅር አመሰግናለሁ የሚለው ሳዳት ጀማል፤ ወደ ውጭ ሄዶ ለመታከም አቅም የሌለኝ በመሆኑ ሁሉም ሰው የሚችለውን ድጋፍ ያድርግልኝ ሲልም ከኢቢሲ ዶትስትሪም ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል፡፡

“ሕዝቡ ያሳየኝ ፍቅር  ለሀገር አንድ ነገር እንደሰራሁ እና እንዳበረከትኩ እንዲሰማኝ አድርጎኛል፤ የኢትዮጵያ ሕዝብም እንደሚያሳክመኝ እምነትም አለኝ” ብሏል፡፡

ሳዳት ጀማል ጤናው ተመልሶ ታዳጊዎችን በማፍራት ለእግር ኳሱ አሁንም አንድ ነገር የማበርከት ጉጉት እንዳለውም ተናግሯል።

 

በላሉ ኢታላ

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ

ተያያዥ ዜናዎች: