በመሠረተ ልማት፣ በኮሪደር ፕሮጀክቶች፣ በተቋማዊ ለውጥ እና በዜጎች የሥራ ባህል ግንባታ ኢትዮጵያን ወደ ዘላቂ ብልጽግና ለማሸጋገር የሚደረጉ ጥረቶች እየተጠናከሩ ናቸው።
በመደመር እሳቤ የሚከናወኑ የከተማ እና የገጠር ልማት ሥራዎች የአካባቢዎችን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ የሥራ ዕድልን ለማስፋት፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን ለማነቃቃት እና ለቀጣይ ትውልድ የተሻለች ሀገር ለመገንባት የሚያግዙ መሆናቸው ግልጽ ነው።
በተለይም አዲስ አበባ የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የከተማዋን ገጽታ በመቀየር፣ ለነዋሪዎች ምቹ፣ ንጹሕ እና አረንጓዴ የሕዝብ መገልገያ ስፍራዎችን ለመፍጠር እያገዙ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞ አረንጓዴ ኢኮኖሚን ከዘመናዊ መሠረተ ልማት ጋር የሚያቀናጅ የጫካ ኢኮ-ስማርት ሲቲ ፕሮጀክትም የከተማ ልማትን ከአካባቢ ጥበቃ ጋር ለማስማማት የሚደረገው ጥረት አካል ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች የመሠረተ ልማት ክፍተቶችን ከመዝጋት ባለፈ፣ ሥራ አጥነትን ለመቀነስ እና ዘላቂ የኢኮኖሚ ዕድገትን ለመደገፍ ያላቸውን ሚና አጉልተው ይገልጻሉ።
ፕሮጀክቶቹ በግንባታ ወቅት እና ከተጠናቀቁ በኋላ የሥራ ዕድሎችን ከመፍጠር ባለፈ፣ ወጣቶች ተግባራዊ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ እና በተለያዩ የልማት ዘርፎች እንዲሳተፉ ዕድል እየፈጠሩ መሆኑም አመልክተዋል።
በኮሪደር ልማቱ ምክንያት የቤቶች ግንባታ እንቅስቃሴ መነቃቃቱን እና በአጭር ጊዜ በሺዎች የሚቆጠሩ የመኖሪያ ቤቶች እንዲቀርቡ መሠረት ተጥሏል። በመንገድ መሠረተ ልማት ላይ የተደረጉ ማሻሻያዎችም የጉዞ ጊዜን በመቀነስ፣ የእንቅስቃሴ ቅልጥፍናን እና አጠቃላይ ምርታማነትን ለማሳደግ እያገዙ ይገኛል።
ከአዲስ አበባ ባሻገር በቢሾፍቱ፣ በጅማ፣ በአርባ ምንጭ እና በባሕር ዳር ከተሞች ተመሳሳይ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፣ በሐዋሳም ተጨማሪ ፕሮጀክቶች እየተተገበሩ ናቸው። ይህም የከተማ ልማትን በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ለማስፋፋት እና ለተመጣጠነ ዕድገት ለመሥራት የሚደረገውን ጥረት ያመለክታል።
በሌላ በኩል የመንገድ፣ የኢነርጂ፣ የሎጂስቲክስ እና የአቪዬሽን መሠረተ ልማቶች ለሀገራዊ ኢኮኖሚ ዕድገት እና ለክልላዊ ትሥሥር ወሳኝ ናቸው። እነዚህ መሠረተ ልማቶች የሚኖራቸው ዘላቂ ጠቀሜታ ግን በተቋማዊ አቅም፣ በብቃት አስተዳደር እና በዜጎች የመጠበቅ ባህል ሲደገፉ ነው።
በዚህ ረገድ በዲጂታላይዜሽን የታገዘ የአገልግሎት አሰጣጥ፣ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎቶች መስፋፋት እና የታክስ ሥርዓት ዘመናዊነት የተቋማዊ ለውጡ አካል ናቸው።
የአካላዊ ልማትን ከዕውቀት፣ ከማኅበራዊ ንቃተ ኅሊና እና ከሥነ ምግባር ጋር ማቀናጀትም የልማት ውጤቶችን ለማስቀጠል ወሳኝ እየሆነ ነው።
በተለይም ሌብነትን እና ሙስናን የሚቃወም፣ ጊዜን በአግባቡ የሚጠቀም፣ በላቡ እና በዕውቀቱ የሚተማመን እንዲሁም የመጪውን ትውልድ ዕጣ ፈንታ የሚያስብ ዜጋ መገንባት የዘላቂ ብልጽግና መሠረት ነው።
በአጠቃላይ በመሠረተ ልማት፣ በከተማ ልማት፣ በተቋማዊ ለውጥ እና በዜጎች ክህሎት እና ሥነ ምግባር ላይ የሚደረጉ የተቀናጁ ጥረቶች ኢትዮጵያ የኢኮኖሚ፣ የምግብ እና የቴክኖሎጂ ሉዓላዊነቷን ለማጠናከር የምታደርገውን ጉዞ ይደግፋል።
ልማቱን በዕውቀት፣ በሥራ ባህል እና በሥነ ምግባር ማጠናከር የሀገራችንን የወደፊት ብልጽግና ለማረጋገጥ ወሳኝ ነው።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: