Search

የትውልድ ግንባታ ለሀገራዊ ከፍታ፦ የመደመር መንግሥት የረጅም ጊዜ ርዕይ እና የልማት መንገድ

ማክሰኞ ጥቅምት 17, 2019 56

አንድ ሀገር የምታስመዘግበው ጊዜያዊ የኢኮኖሚ ዕድገት ብቻውን የዘላቂ ሥልጣኔ ማረጋገጫ ሊሆን አይችልም። ዘላቂ ሀገራዊ ከፍታ የሚረጋገጠው የዛሬን ጥቅም አርቆ ከመመልከት ጋር በማስማማት፣ ለነገው ትውልድ የሚተርፍ ጠንካራ መሠረት ሲጣል ነው።

የመደመር መንግሥት የልማት እና የሥልጣኔ ጉዞው የከፍታ ጥግ አድርጎ የያዘው ዋና ዓላማ የራሱን ፍላጎት ከሀገር እና ከትውልድ የጋራ ጥቅም ጋር ማስማማት የሚችል፣ ኃላፊነት የሚሰማው እና የረጅም ጊዜ ርዕይ ያለው ዜጋ መፍጠር ነው።

የትውልድ ግንባታ ከቁሳዊ ልማት እና ከተቋማዊ ዕድገት የሚነጠል ሳይሆን፣ የሁሉም ሀገራዊ እንቅስቃሴዎች ማዕከል እና የመጨረሻ ግብ እንዲሁም በሁሉም የልማት መስኮች ውስጥ የሚንጸባረቅ የተቀናጀ ሂደት ነው።

የመደመር ዕይታ እነዚህን የልማት ምሰሶዎች ከሰው ሀብት ልማት ጋር ሲያያይዝ፤ የመንገድ፣ የባቡር፣ የኤሌክትሪክ እና የዲጂታል መሠረተ ልማቶች መስፋፋት የዛሬን የንግድ እና የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ከማሳለጥ ባለፈ፣ መጪው ትውልድ በቀላሉ የሚገናኝበት እና አቅሙን የሚያወጣበትን ሰፊ አውድ ይፈጥራል።

ትምህርትን ከንድፈ ሐሳብ ባለፈ ከተግባራዊ የቴክኖሎጂ እውቀት ጋር ማጣመር ትውልዱ ከዓለም አቀፍ የዕድገት ደረጃ ጋር እንዲራመድ እና የራሱን የፈጠራ መፍትሔዎች እንዲያመጣ ያስችለዋል።

እንዲሁም ጠንካራ እና ገለልተኛ ተቋማትን መገንባት ለዜጎች እኩል የዕድል አድማስ የሚፈጥር ሲሆን፣ የሥራ ፈጠራ አመለካከትን ማሳደግ ደግሞ ትውልዱ ከጠባቂነት ተላቅቆ የሀገር ሀብት ፈጣሪ እንዲሆን ያደርጋል።

በአሁኑ ወቅት የሚከናወኑ ታላላቅ ሀገራዊ የልማት እንቅስቃሴዎች የዛሬን ፍላጎት ከመመለስ በላይ ለነገው ትውልድ የተሻለ የኑሮ መሠረት እና የተረጋጋ ሀገራዊ አውድ እየፈጠሩ ይገኛሉ።

ለአብነትም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር የችግኝ ተከላ እንቅስቃሴ የአፈር መሸርሸርን ከመከላከል እና የአየር ንብረት ለውጥን ከመቋቋም ባለፈ፣ የመጪው ትውልድ የውኃ እና የምግብ ዋስትና እንዲረጋገጥ፣ የተፈጥሮ ሀብት እንዲጠበቅ የሚያደርግ የረጅም ጊዜ ኢንቨስትመንት ነው።

በተመሳሳይ እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች መጪው ትውልድ በራስ የመተማመን መንፈስ እንዲኖረው እና የበለጸገች ሀገር እንዲረከብ መንገድ ይከፍታሉ።

የከተሞች ኮሪደር ልማት እና የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ደግሞ ከተሞችን ለኑሮ ምቹ፣ ጽዱ እና ዘመናዊ ማድረግ እንዲሁም የዲጂታል አሠራርን ማስፋፋት ለቀጣዩ ትውልድ የተቀናጀ እና የጸና የኢኮኖሚ አውድ ያመቻቻሉ።

ሀገራዊ ከፍታን ለማረጋገጥ የዜጎች አስተሳሰብ መገንባት ወሳኝ ድርሻ አለው። ዜጋን በዕለታዊ እና ጊዜያዊ ፍላጎት ብቻ ከመመራት ወደ አርቆ አስተዋይነት ማሸጋገር፣ የግል ፍላጎትን ከሀገር እና ከማኅበረሰብ ዘላቂ ጥቅም ጋር በማጣጣም ግጭቶችን በመቀነስ ሰላም እና መረጋጋትን ያጠናክራል።

የትውልድ ግንባታ የመንግሥት ብቻ ኃላፊነት ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። ይልቁንም የሁሉም ባለድርሻ አካላት የጋራ ርብርብ የሚጠይቅ ሀገራዊ ተልዕኮ ነው። ቤተሰብ የቅንነት፣ የኢትዮጵያዊነት እሴቶች እና የመልካም ሥነ ምግባር የመጀመሪያው ማነጻጸሪያ እና መሠረት ነው።

የትምህርት ተቋማት እውቀትን ከግበረ ገብነት ጋር በማቀናጀት አቃፊ እና አርቆ አስተዋይ ዜጋን የመቅረጽ ኃላፊነት አለባቸው። እንዲሁም ማኅበረሰብ እና የግሉ ዘርፍ ማኅበራዊ ደኅንነትን ከመጠበቅ ባሻገር፣ ለወጣቶች የሥራ እና የፈጠራ ዕድሎችን በመክፈት የኢኮኖሚ ተሳትፏቸውን ያረጋግጣሉ። በመሆኑም እያንዳንዱ ዜጋ የራሱን ድርሻ ጠንቅቆ በመረዳት ለሀገር ዕድገት እና ለጋራ ደኅንነት በኃላፊነት የመንቀሳቀስ ግዴታ ይኖርበታል።

የመደመር መንግሥት የልማት ፍልስፍና ዋና ማዕከል የዛሬን ፍላጎት እያሟሉ ለነገው ትውልድ የተሻለች እና የተረጋጋች ሀገር ማቆየት ነው። የልማት፣ የቴክኖሎጂ፣ የመሠረተ ልማት እና የተቋማት ግንባታ ጥረቶች ስኬታማ የሚሆኑት አርቆ የሚያስብ፣ ኃላፊነት የሚሰማው እና የጋራ ጥቅምን የሚያስቀድም ዜጋ ሲገነባ ነው።

የትውልድ ግንባታን የጋራ ተልዕኮ በማድረግ የሚከናወኑ የልማት ተግባራት ደግሞ የሀገራችንን የሥልጣኔ እና የከፍታ ጉዞ ዘላቂ እንደሚያደርጉት አይቀሬ ነው።

በአድማሱ አራጋው

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: