ከተሞቻችን ለሰዎች እንጂ ለሕንፃዎች ብቻ የሚገነቡ አይደሉም፡፡ በከተሞቻችን ሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች መኖራቸው ባይከፋም፣ የነዋሪዎቻቸውን ምቾት እና ደኅንነት ከግምት ማስገባት ግድ ይላል፡፡
ለዚህ ነው የመደመር መንግሥት በአዲሱ ዘመን ዕሳቤ ከተሞች ለመኖሪያ ምቹ፣ ለንግድ ማሣለጫ፣ ለፈጠራ እና ለቢዝነስ መጀመሪያና መጎልበቻ፣ ለቱሪስት ምቹ ሆነው ሊቆረቆሩ እንደሚገባ አቅዶ እየተገበረ የሚገኘው፡፡
ከተሞች የመኖሪያ፣ የንግድ፣ የአረንጓዴ እና የመዝናኛ ሥፍራዎችን በጥምር ያካተቱ እንዲሆኑ በማድረግ ረገድ አዲስ አበባን ጨምሮ በክልል ከተሞች ለኑሮ ምቹ፣ ውብና ለነዋሪዎቻቸው የሚመጥኑ ተጨባጭ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡
በኮሪደር ልማት ለሰዎች ተስማሚ የሆኑ የእግረኛ መንገዶች፣ የብስክሌት መተላለፊያዎች፣ አረንጓዴ ቦታዎች እና የመዝናኛ ፓርኮች ተገንብተዋል።
በከተሞች ውስጥ ባሉ ክፍት ቦታዎች፣ በወንዝ ዳርቻዎች እና በመንገዶች ዳር የሚደረጉ የልማት ሥራዎች የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ባለፈ የከተሞቹን ውበት ከፍ አድርገዋል።
በወንዝ ዳርቻ ልማቶች ከተሞችን ከብክለት በማጽዳት ለሕዝብ ማረፊያ እና መዝናኛነት እንዲመቹ ሆኗል።
በከተሞች ልማት ዘርፍ የተከናወኑት እነዚህ ሥራዎች የሀገራችንን ገጽታ በመቀየር፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን በማነቃቃት እና ለዜጎች ምቹ የመኖሪያና የሥራ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ ከፍተኛ ለውጦችን አሳይተዋል።
ይህ ታላቅ ርዕይ ሀገራችን በሕዝቧ እና በታሪኳ ግዝፈት ልክ እንድትራመድ ያስቻለ ትልቅ የአመራር ጥበብ የታየበት ክንውን ነው።
የኢትዮጵያ ትልቁ ፈተና የሀብት እጥረት ሳይሆን፣ የነበረውን የተፈጥሮና የሰው ኃይል በአግባቡ አቀናጅቶ ለመጠቀም የሚያስችል የአስተሳሰብ እና የርዕይ ችግር ብቻ እንደነበር አሁን የተመዘገቡት ስኬቶች በግልጽ አሳይተዋል።
የ“አንችልም” ትርክትን ሰብሮ ዓለምን ያስደነቁ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም ማሳካት መቻሉም የዚህ ማሳያ ነው። የኢትዮጵያን ከተሞች የሰላም፣ የብልጽግና እና የዘመናዊነት ተምሳሌት ለማድረግ የተጀመሩት የልማት እርምጃዎችም ተጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
በዓይናለም ሃድራ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: