የሀገር ግንባታ ሂደት ከቀላል አስተዳደራዊ ወይም ፖለቲካዊ መዋቅር ፈጠራ በላይ የሆነ፣ የትውልዶችን ጥረት፣ መስዋዕትነት እና የጋራ ራዕይ የሚጠይቅ ጥልቅ ታሪካዊ ጉዞ ነው።
በኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ውስጥ በርካታ ውጣ ውረዶችና ድሎች ተመዝግበዋል። ይሁን እንጂ የሀገርን ከፍታ ከህልም ወደ እውን እጅግ በተጨባጭ ለመለወጥ የዕድገት ጉዞው መሠረት መሆን የሚገባው አንድ ወሳኝ እውነት አለ፤ እርሱም ሀገር የምትገነባው ከዳር ሆኖ አስተያየት ከሚሰጡ ተመልካቾች ሳይሆን፣ ዕጣ ፈንታቸውን በገዛ እጃቸው ለመቅረጽ ኃላፊነትን በሚወስዱ ባለቤቶች መሆኑ ነው።
ይህ ሐሳብ በመደመር መንግሥት ውስጥ በጉልህ የሚንጸባረቅ ሲሆን ዜጎች ከባለቤትነት መንፈስ በመነሳት ሀገራዊ አቅማቸውን የሚያቀናጁበትን መንገድ ያመላክታል ደግሞም አበክሮ በተግባር ያሳያል።
የኢትዮጵያ የልማትና የብልጽግና ጉዞ ትልቁ ፈተና የሀብት እጥረት ሳይሆን፣ የተበታተነ አቅምን በአግባቡ ባለማስተባበር የሚፈጠር የመዋቅር ክፍተት መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተጻፈው የመደመር መንግሥት መጽሐፍ ላይ ተገልጿል።
"የዓባይን ልጅ ውኃ ጠማው" የሚለው አባባል የሚያስታውሰን ይህንኑ የኢትዮጵያ የሀብት እና የአቅም ለየብቻ በአንድ ቦታ የመገኘት ተቃርኖ ነው።
ሀገር በጸጋ የታደለች ብትሆንም ዜጎች ተመልካች ብቻ እስከሆኑ ድረስ ጸጋው ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና ሊለወጥ አይችልም። ለዚህም ነው የመደመር መንግሥት የዓባይን ልጅ ውኃ ለምን ጠማው ብሎ የሚጠይቀው። ይህ ጥያቄ ደግሞ ሀብት እና የተበታተነ አቅም ለየብቻ መሆናቸውን እንድንገነዘብ ያደርጋል።
ጥያቄውንም ወደሥራ ሲተረጉመው የተበታተነውን አቅም አሰባስቦ በሃብቱ ላይ በማፍሰስ የዓባይን ልጅ ውኃ ለምን ጠማው? ከሚለው ጥያቄ አውጥቶ መፍትሄውን ሰርቶ ያሳያል። ይህ ነው የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴን ገንብቶ የብልጽግና ተምሳሌት የተበጣጠሱ አቅሞች ተደምረው ግዙፍ ሃብት እንደሚፈጥሩ በተግባር ተርጉሞ ጉባ ላይ የሚያሳየን።
እዚህ ላይ ታዲያ ዜጋው በሂደቱ ውስጥ ያለው ተሳትፎ ከገለልተኛ ወይም የዳር ተመልካችነት ከሆነ የህዳሴን የመጨረሻ ውጤት አያመላክተንም ነበር፤ ለዛም ነው ዜጎች ሁሉ ንቁ የባለቤትነት ስሜት እንዲያድርባቸው እና የጉባ አሻራቸውን እንዲያኖሩ የተደረገው።
ዜጎች ሀገራቸው እንደ የቤት ባለቤትነት የሚንከባከቧት ሲሆኑ ብቻ ተቋማት ይጠነክራሉ፣ ኢኮኖሚውም እሴት ማመንጨት ይጀምራል። እዚህ ላይ የኑረዲን ኢሳ ግጥም ጥሩ ምሳሌ ትሆናለች፦
"ይሄ ምናገባኝ የምትሉት ሀረግ፤
እሱ ነው ሀገሬን ያረዳት እንደበግ"
የሚል ግጥም ልጽፍ አሰብኩና፤
ምናገባኝ ብዬ ተውኩት እንደገና።"
በሚሉት ስንኞች ውስጥ በሀገር ጉዳይ ላይ “ምን አገባኝነት” ስሜት ሀገርን ለከፋ ችግር እንደሚዳርግ ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦ፣ እሱም ግን እንደገና የአባባሉ ሰለባ መሆኑን ይነግረናል።
እንዲህ ያለው የ”ምን አገባኝ”ነት ሰለባ መሆን በሀገር ውስጥ ለተበጣጠሱ አቅሞች መፈጠር ምክንያት መሆኑ አይቀርም። ይህ ደግሞ ሀብትን እያዩ በቁጭት ወይም ሀብትን ወደ አቅም የመመለወጥ አቅም ሰለባ ያደርጋል። ሀብት እያለ በተበጣጠሰ አቅም ውስጥ መኖር ህልምን አያሳካም።
ለዚህም ነው አሁን ኢትዮጵያ የጀመረችው ሰፊ የልማት፣ የማሻሻያ እና የብሔራዊ አቅም ግንባታ ጉዞ ማዕከሉ ይህንኑ የባለቤትነት ፍልስፍና ያደረገው።
ታሪክ እንደሚያስተምረን ከድህነት እና ከኋላቀርነት ተላቀው በአጭር ጊዜ ውስጥ እጅግ የገሰገሱ ሀገራት (እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ሲንጋፖር እና ሩዋንዳ) የስኬታቸው ምስጢር የተመልካቾችን ባህል ሰብረው በሕዝባቸው የባለቤትነት አዕምሮ ላይ የተመሰረተ የዕድገት ሞዴል መከተላቸው ነው።
የሲንጋፖር እና የደቡብ ኮሪያ ሀገራት በፈጣን የኢኮኖሚ ሽግግር ወቅት ዜጎቻቸው በሀገራዊ ምርታማነትና በዕውቀት ሽግግር ውስጥ ንቁ ባለቤቶች እንዲሆኑ አድርገዋል። መንግሥት መድረክ ሲፈጥር፣ ሕዝቡ ደግሞ በዲሲፕሊንና በጠንካራ ሥራ የሀገሪቱን ከፍታ እውን አድርጎታል።
ባለፉት ዓመታት በኢትዮጵያ የተከናወኑ እንደ አረንጓዴ አሻራ ያሉ ግዙፍ ብሔራዊ ተግባራት ማሳያ የሚሆኑት፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ከዳር ተመልካች በመውጣት የሀገራቸው አካባቢያዊ ዕድል ባለቤቶች በመሆን ያከናወኗቸው ታላላቅ ስኬቶች ናቸው። ይህ የሚያሳየው የባለቤትነት ስሜት ሲኖር የማይቻል የሚመስል ነገር እንደሌለ ነው።
እናም ኢትዮጵያ አሁን የያዘችው የዕድገት እና የብልጽግና ጉዞ ስኬት የሚወሰነው በፖለቲካ መሪዎች ብዛት ወይም በጸጋዎች ብቻ ሳይሆን፣ እያንዳንዱ ዜጋ ሀገሩን እንደራሱ ንብረት ተንከባክቦ በመያዝ፣ ከሰነፍ ተመልካችነት ወጥቶ የለውጡ ባለቤት በመሆን በሚያሳየው ቁርጠኝነት ነው።
"እውን የሆነች ሀገር የምትገነባው በተመልካቾች ሳይሆን በባለቤቶች ነው።" ይህ ሐሳብ የኢትዮጵያን የነገ ብልጽግና እውን ለማድረግ የሁላችንንም የዕለት ተዕለት ተግባር ሊመራ የሚገባው ብሔራዊ መርህ ሊሆን ይገባል።
በጌቱ ላቀው
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: