Search

በመቐለ ከተማ ትምህርት ቤቶች ዳግም በመከፈታቸው ተማሪዎች እና መምህራን ደስታቸውን ገለጹ

ማክሰኞ ጥቅምት 17, 2019 45

በታላቅ ጉጉት እና ናፍቆት ሲጠብቁት የነበረው የትምህርት ገበታ ዳግም በመከፈቱ የመቐለ ከተማ ተማሪዎች እና መምህራን የተሰማቸውን ከፍተኛ ደስታ ገለጹ።

በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋት እና ጦርነት ምክንያት ለወራት ከትምህርት ገበታቸው ርቀው ለመቆየት የተገደዱት የመቐለ ከተማ ተማሪዎች፣ አሁን ላይ ሰላም በመስፈኑ እና ወደ ተናፈቀው ትምህርት ቤታቸው በመመለሳቸው ትልቅ እፎይታ አግኝተዋል።

ለኢቲቪ አስተያየታቸውን የሰጡ ተማሪዎች “ፖለቲካ እና ጦርነት እኛን በጣም ጎድቶናል፤ እኛ አሁን ሰላም እና ትምህርታችንን ብቻ ነው የምንፈልገው” ሲሉ መሻታቸውን ገልጸዋል።

ትምህርት አቋርጠው በመቀመጣቸው የሥነ ልቦና ጉዳት ደርሶባቸው እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ከጓደኞቻቸው ጋር ዳግም በመገናኘታቸው ለነገ ብሩህ ተስፋቸው አዲስ መንገድ መከፈቱን ጠቁመዋል።

የትምህርት ቤቶቹ ዳግም መከፈት ከተማሪዎች በተጨማሪ መምህራንንም በእጅጉ አስደስቷል።

የአጼ ዮሐንስ ትምህርት ቤት መምህር የሆኑት ደረጀ አድማሱ፣ ተማሪዎች ከትምህርታቸው ሲፈናቀሉ የሚያመጣው የሥነ-ልቦና ጫና ከባድ እንደነበር አንስተዋል።

ሕፃናቱ አላስፈላጊ ሁኔታዎች ላይ ከመሰማራት ድነው አሁን በክፍል ውስጥ እውቀት እና ሥነ-ምግባር በመቅሰም ላይ መሆናቸው ትልቅ እረፍት እንደሰጣቸው እና ተማሪዎች በደስታ እየተማሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የአጼ ዮሐንስ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ሮቤል ተስፋ ሥላሴ በበኩላቸው፣ በአጥፊው የህወሓት ቡድን ጥቃት በትምህርት ቤቶች ላይ በደረሰው ውድመት ምክንያት ተቋማቱ በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እንዳይሰጡ እንቅፋት መኖሩን ተናግረዋል።

በተለይም ቀደም ሲል የነበሩ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኮምፒውተሮች እና ላፕቶፖች አሁን ላይ ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ነው የገለጹት።

መንግሥት የትምህርት መሣሪያዎችን እና ቁሳቁሶችን ዳግም በመተካት ድጋፍ እንዲያደርግ የትምህርት ማኅበረሰቡ ጥሪ አቅርቧል።

አሁን ላይ በትግራይ ክልል አስተማማኝ ሰላም በመስፈኑ፣ ወላጆች ትናንት ትምህርት ሲናፍቁ የነበሩ ልጆቻቸውን ዳግም ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲልኩ ጥሪ ቀርቧል።

የባለ አደራው አስተዳደር እና የመደመር መንግሥት ፈጣን ምላሽም ለዜጎች የነገ ብሩህ ተስፋ እንደ አዲስ የሚያለመልም መሆኑ ተመላክቷል።

#ትልቅሀገር #ትልቅሕዝብ #ታላቅርዕይ

በሜሮን ንብረት

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: