Search

ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን ፀረ-ሕዝብ መሆን እና ኋላ ቀር አስተሳሰብ መገለጫዎቹ ናቸው

ማክሰኞ ጥቅምት 17, 2019 51

ሕገ ወጡ የህወሓት ቡድን የሕዝብ ሀብት እና ምልክት የሆኑ ተቋማት ላይ ውድመት በማድረስ የሕዝብ ጠላት መሆኑን በተደጋጋሚ በሚሠራቸው እኩይ ተግባር አስመስክሯል።

ሰሜን ዕዝን በማጥቃት ሀገር ላይ ከባድ ክህደት የፈፀመው ቡድኑ ለመከላከያ ሠራዊት እንደ ትዕምርት የሚቆጠረውን የሰሜን እዝ ዋና መምሪያ ቢሮ ሕንፃዎች እና መሠረተ-ልማቶች ለአገልግሎት የማይመቹ እና ከጥቅም ውጪ እንዲሆኑ አድርጏል።

ሀገርን ለማፍረስ ሲንቀሳቀስ የቆየው የኋላ ቀሩ የህወሓት ቡድን፣ የሰሜን ዕዝን በወረራ በቁጥጥሩ ሥር ባደረገባቸው ጊዜያት የፈጸማቸው አስነዋሪ ድርጊቶች የቡድኑን የከፋ ባሕርይ የገለጡ ናቸው።

የሕንፃ ቢሮ ክፍሎች እና ንብረቶች ሆን ተብሎ እንዲወድሙ ተደርጓል። ታሪካዊ እና ሀገራዊ ግርማ ሞገስ ያላቸውን ተቋማት ሆን ብሎ ማዋረድ እና ማሳነስ የጥፋት ቡድኑ መለያ መሆኑን ሂደቱ አሳይቷል።

ይህ ቡድን በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ያለውን ጥልቅ ጥላቻ እና ንቀት በተደጋጋሚ በግልጽ ያሳየ ሲሆን፣ ከዕለት ዕለት የሚፈጽማቸው ፀረ-ሕዝብ ድርጊቶችም የባንዳነት እና የውጭ ተላላኪነቱ ፍፁም መገለጫው ሆነዋል።

የሕዝብን እና የሀገርን ክብር የማይመጥን፣ ለትውልድ የሚተርፍ ታሪካዊ ፀፀት የሚያስከትል ተግባር መፈፀሙ የቡድኑን ፖለቲካዊ እና ሞራላዊ ውድቀት የያመላክት ነው።

የሰሜን ዕዝ ዋና ማዘዣ ቢሮ መዋቅር ላይ የደረሰው ጉዳት የቁሳቁስ ብቻ ሳይሆን፣ የቡድኑን ኋላ ቀር አስተሳሰብ እና የጥፋት ዕሳቤ በግልጽ ያሳየ ክስተት ነው።

ሕዝቡ እና መንግሥት ይህንን የቡድኑን የጥፋት አካሄድ በጽኑ የሚኮንኑት ሲሆን፣ የደረሰውን ውድመት በዘላቂነት በመጠገን እና ተቋማዊ ክብሩን በመመለስ ረገድ የሁሉንም አካላት የተቀናጀ ርብርብ የሚጠይቅ መሆኑ ተመላክቷል።

በወንድወሰን አፈወርቅ

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: