Search

ከመጓተት ወደ ተግባራዊ ውጤት፦ የኢትዮጵያ ሜጋ ፕሮጀክቶች አዲስ የአፈጻጸም ምዕራፍ

ማክሰኞ ጥቅምት 17, 2019 49

ኢትዮጵያ በቀደሙት ዓመታት የጀመረቻቸው ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች በአፈጻጸም መጓተት፣ በአስተዳደር ማነቆዎች እና በሃብት ብክነት ምክንያት ከተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ዘግይተዋል። አንዳንዶቹ ከመሠረት ድንጋይ ውጪ ወደ ተግባር ሳይሸጋገሩ ሲቀሩ፣ ሌሎች ለዓመታት በመጓተታቸው ተጨማሪ ወጪ እና ኪሳራ አስከትለዋል።

ይሁን እንጂ የመደመር መንግሥት የፕሮጀክቶች አፈጻጸም ባህልን በመቀየር፣ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን ከውድቀት መታደግ እና አዳዲስ ሜጋ ፕሮጀክቶችን በማቀድ ብቻ ሳይገደብ ወደ ተግባር በመቀየር ሀገራዊ ፋይዳ እንዲኖራቸው እያደረገ ነው።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ የኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ እና የመገጭ መስኖ ግድብ የዚህ ሂደት ዋና ማሳያዎች ናቸው።

በብዙ ፈተናዎች ውስጥ ያለፈው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ፣ በመጀመሪያ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳና በጀት እንዳይጠናቀቅ ተግዳሮቶች ገጥመውት ነበር። ይሁን እንጂ በአፈጻጸም ድክመቶች እና በአስተዳደር ችግሮች የተፈጠሩ ማነቆዎችን ለመፍታት በተወሰዱ እርምጃዎች የግንባታ ሂደቱ ወደ ፍጻሜ ሊደርስ ችሏል።

በተለይም የመደመር መንግሥት የሰጠው ከፍተኛ ትኩረት፣ የአመራር ቁርጠኝነት እና ቀጣይነት ያለው ክትትል የጎላ ሚና ተጫውቷል።

በተመሳሳይ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሚገኘው የኮይሻ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ ፕሮጀክት ከተጀመረ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች ተጓትቶ ቆይቷል። በተሰጠው ልዩ ትኩረት እና በተወሰዱ የማስፈጸሚያ እርምጃዎች የግንባታ ሂደቱ ተፋጥኖ እየተጠናቀቀ ይገኛል።

ሌላኛው ግዙፍ ፕሮጀክት የሆነው እና በኮንትራክተሩ የአፈጻጸም አቅም ማነስና በሌሎች ተግዳሮቶች ምክንያት ለዓመታት የተጓተተው የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት፣ አሁን ላይ በተወሰዱ የማስፈጸሚያ እርምጃዎች የግንባታ ሂደቱ ተጠናቅቆ በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።

ከእነዚህ ፕሮጀክቶች ባለፈ በቱሪዝም መዳረሻዎች፣ በኮሪደር ልማት፣ በኢንዱስትሪ ማስፋፊያና በሌሎች ዘርፎች የሚከናወኑ ሥራዎች የሀገራችንን የመፈጸም አቅም ለማሳደግ የሚደረጉ ጥረቶች አካል ናቸው።

አዳዲስ የኢንዱስትሪ ፕሮጀክቶችን በማቋቋምና ወደ ምርት በማስገባት የሥራ ዕድል ለመፍጠር፣ የሀገር ውስጥ ምርትን ለማሳደግ እና የኢኮኖሚ መሠረትን ለማጠናከር የሚደረጉ ጥረቶችም ከፍተኛ ትኩረት አግኝተዋል።

የመደመር መንግሥት አሁን ላይ አቅዶ ተግባራዊ እያደረጋቸው የሚገኙ እንደ ቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ፣ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ፣ የማዳበሪያ ፋብሪካ፣ የተፈጥሮ ጋዝ ልማትና የነዳጅ ማጣሪያ ያሉ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶች እንዲሁም የዜጎችን የቤት ፍላጎት ለማሟላት የተያዙ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ዕቅዶች የኢኮኖሚ ዕድገትን፣ የሥራ ዕድልን እና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል።

በመሆኑም የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ከመጓተት መታደግ፣ የሀብት ብክነትን መቀነስ፣ የአፈጻጸም አቅምን ማጠናከር እና አዳዲስ ፕሮጀክቶችን በጥራት ማጠናቀቅ የሀገራዊ ልማት ዋና መሠረቶች ናቸው።

ሀገርን ወደ ብልጽግና ለማሸጋገር ማቀድና መጀመር ብቻ ሳይሆን፣ የተጀመረውን ሥራ በተያዘለት ጊዜ፣ በተፈለገው ጥራት እና በሚጠበቀው ሀገራዊ ፋይዳ ማጠናቀቅ ወሳኝ ነው።

በኢንቲሃድ አብራር

 

አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: