የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ በ3ኛው የሳይበር ደኅንነት ወር ኮንፈረንስ እና አውደ ርዕይ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የባንክ አገልግሎት በተለይም ዲጂታል የባንክ አገልግሎት መሠረት የደንበኞች እምነት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተውበታል።
ከ48 ሚሊዮን በላይ ደንበኞች፣ ከሀገራዊ ዓመታዊ 30 ትሪሊዮን ብር በላይ ዲጂታል ግብይት የ22 ትሪሊዮን ብር ግብይት፣ ከ92 በመቶ በላይ ዲጂታል ግብይት በባንክ ደረጃ እንዲሁም ከአጠቃላይ ሀገራዊ ዲጂታል ግብይት 73 በመቶ የሚሆነው በባንኩ ዲጂታል የአገልግሎት አማራጮች የሚፈጸም መሆኑን አቶ አቤ ተናግረዋል።
ይህ በትልልቅ ቁጥሮች የተገለጸው አፈጻጸም የስኬት መገለጫ ብቻ ሳይሆን፣ ይልቁንስ በደንበኞቹ የተጣለብንን አደራ ግዝፈት ማሳያ መሆኑን ነው አቶ አቤ ያሰመሩበት።
የሳይበር ደኅንነትን ማረጋገጥ ማለት የደንበኞችን መተማመን መጠበቅ፣ አገልግሎቶችን አስተማማኝ ማድረግ እንዲሁም ዲጂታል የባንክ አገልግሎትን ዕድገት ማረጋገጥ መሆኑን ባንኩ እንደሚረዳ የገለጹት አቶ አቤ፣ “ደኅንነቱ የተጠበቀ እና ስጋቶችን በሚገባ የሚረዳ ባንክ” ከባንኩ የስትራቴጂ ምሰሶዎች አንዱ መሆኑን ተናግረዋል።
ደንበኞቹ በጣሉብን እምነት ልክ ለመገኘት ባንኩ ሰባቱን ቀናት ለ24 ሰዓት የሳይበር ደኅንነቱን የሚጠብቅበት ሥርዓት መዘርጋቱን የገለጹት አቶ አቤ፣ ለዚህ ዓላማ የሚወጣው ከፍተኛ ወጪ የደንበኞችን እምነት በማጣት ከሚደርስብን ጉዳት ጋር አይነጻጸርም ብለዋል።
የሳይበር ደኅንነት ስጋቶች ዓይነት በየጊዜው እየተለዋወጠ እንደመጣ እና በተለይ አሁን የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዕድገት ለጥቃት አድራሾች ምቹ ሁኔታን እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል።
ባንኩ በየጊዜው ለሚለዋወጠው የጥቃት ዓይነት ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት አስቀድሞ እንደሚዘጋጅ የገለጹት አቶ አቤ፣ በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ የታገዘ መከላከያ ሥርዓት በባንኩ እየተገነባ እንዳለ እና ማንም ይሁን ምን አስቀድሞ በአግባቡ ካልተረጋገጠ በስተቀር ከሳይበር ደኅንነት ጋር ተያይዞ እምነት ያለመጣል አሠራር እንደተተገበረ ገልጸዋል።
ባንኩ በዘረጋው ጠንካራ የደኅንነት ሥርዓት ባለፈው ዓመት ብቻ ከ14 ሺህ በላይ በመሠረተ ልማቶቻችን ላይ የተቃጣ ጥቃት እና ሌሎች ጥቃቶችን መከላከል መቻሉን አቶ አቤ ተናግረዋል።
ቴክኖሎጂ ብቻውን ደኅንነትን እንደማያረጋገጥ የገለጹት አቶ አቤ፣ እርምጃ ከመውሰድ በፊት ቆም ብሎ በማሰብ፣ ከማመን በፊት በማረጋገጥ ሠራተኞች ደንበኞችንም ራሳቸውንም፣ ደንበኞችም ራሳቸውን ከጥቃት መከላከል እንደሚገባቸው አሳስበዋል።
አንድ ተቋም የቱንም ያህል ጠንካራ የደኅንነት ሥርዓት ቢዘረጋ ብቻውን ደኅንነቱን ማረጋገጥ እንደማይችል የገለጹት አቶ አቤ፣ ባንኩ ይህን በማመኑ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር ትብብር ለመፍጠር እና በጋራ ለመሥራት ነው የግንዛቤ መስጫ ወሩን ያዘጋጀው ብለዋል።
የሁለቱ ቀናት ጉባኤ ዓላማ ይሄው መሆኑን የገለጹት አቶ አቤ፣ ለደንበኞች እና ለሠራተኞች ግንዛቤ መስጠት፣ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጪ የትብብር ማዕቀፍ መፍጠር፣ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ስለ አዳዲስ ስጋቶች ማወቅ እና ከዘርፉ ባለሙያዎች፣ ከአምራቾች እና አቅራቢዎች ተግባራዊ ተሞክሮዎችን መውሰድ እንደሚጠበቅ ገልጸው፣ መርሐ ግብሩ በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ ያላቸውን ምኞት ገልጸዋል።
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: