የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች ያስገነባቸውን 11 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን አስመርቋል።
ተቋሙ በቢሸፍቱ፣ ሞጆ፣ አዳማ፣ ባቱ፣ ሀዋሳ ከተሞች እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ አምስት ቦታዎች ያስገነባቸውን የኤሌትሪክ ቻርጅ መሙያ ጣቢያዎችን ነው በዛሬው ዕለት ያስመረቀው።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢ/ር ጌቱ ገረመው በዚሁ ወቅት፣ ኢትዮጵያ ያላትን የታዳሽ ኃይል ሀብት በመጠቀም የአረንጓዴ ኢኮኖሚን እየገነባች እንደምትገኝ ገልጸዋል።
የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ልማት የነዳጅ ጥገኝነትን እና የውጭ ምንዛሪ ወጪን ለመቀነስና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ቀደም በአዲስ አበባ የተገነቡ ጣቢያዎች በአንድ ጊዜ ከ54 በላይ ተሽከርካሪዎችን የማስተናገድ አቅም ፈጥረዋል ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ዛሬ ቢሾፍቱን ጨምሮ በአዲስ አበባ እና በተለያዩ ከተሞች ሥራ የጀመሩት 11 ጣቢያዎች በአንድ ጊዜ ለ96 ተሽከርካሪዎች አገልግሎት የመስጠት አቅም እንዳላቸው አመላክተዋል።
በዚህም አሁን ላይ አገልግሎቱ 14 ጣቢያዎችን የገነባ ሲሆን፣ እነዚህ ጣቢያዎች በአንድ ጊዜ 150 ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ ማድረግ የሚችሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በቀጣይ በተለያዩ ከተሞች መሠል የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች የኃይል መሙያ ጣቢያዎችን ለመገንባት እየተሠራ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ በአነስተኛ ክፍያ ተጠቃሚዎች እነዚህን ጣቢያዎች መጠቀም እንደሚችሉ ገልጸዋል።
የቢሾፍቱ ከተማ ከንቲባ አለማየሁ አሰፋ በበኩላቸው አገልግሎቱ በከተማዋ ያስገነባው 2 የኃይል መሙያ ጣቢያዎች ለከተማዋ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በኢትዮ-ጅቡቲ ኮሪደር ላይ የተቀናጀ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ የኃይል መሙያ ኔትወርክ ለመገንባት የሚደረገውን የጋራ የኢንቨስትመንት አገልግሎቱን ሥራ ለማስጀመር ስምምነት ተፈፅሟል።
በአባዲ ወይናይ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: