በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ታሪካዊና አዲስ የሰላም ምዕራፍ መከፈቱን የሚያበስሩ አበይት ተግባራት ተጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን፣ የቀድሞ ታጣቂዎች ለትግራይ ክልል ሰላም ግንባታና ሁለንተናዊ እድገት የድርሻቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ እያከናወነ በሚገኘው የትጥቅ ማስፈታት፣ የቀድሞ ተዋጊዎችን ከጦር ሜዳ ማስወጣትና ወደ ማህበረሰብ መልሶ የማቀላቀል (DDR) ፕሮግራም እስካሁን በተለያዩ ክልሎች ከ93 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎችን ወደ ሰላማዊ ሲቪል ሕይወት መመለሱን ይፋ አድርጓል።
የትግራይ ታጣቂዎች ትጥቅ ፈትተው ወደ ተሃድሶ ሥልጠና ማስገቢያ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው አስተያየታቸውን የሰጡ የቀድሞ ታጣቂ ተወካዮች በትግራይ ክልል ተከታታይ ጦርነትና የሰላም እጦት ያስከተሉትን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጫናዎች ለማስወገድ ከመንግሥት ጎን በመቆም የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ አደራ ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የብሔራዊ ተሃድሶ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን በበኩላቸው፤ በትግራይ ክልል አዲስ በተመረጡ አምስት ጊዜያዊ የዲሞቢላይዜሽን ማዕከላት ከ47 ሺህ በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች በቅድመ-DDR ምዝገባ ሂደት ማለፋቸውን አብራርተዋል።
ከእነዚህ መካከልም ከ5 ሺህ 500 በላይ የቀድሞ ታጣቂዎች የቅድመ-DDR መስፈርቶችን አሟልተው የምዝገባ ሂደት መጀመራቸውን አስረድተዋል።
የትግራይ ክልል ባለአደራ አስተዳደር የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ብርጋዴር ጄኔራል ገብረእግዚአብሔር በየነ የቀድሞ ታጣቂዎችን ከጦርነት አዙሪት ወጥተው ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንዲመለሱና ለሰላም ግንባታ ግንባር ቀደም አጋር እንዲሆኑ የክልሉ ባለአደራ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የለጋሽ ድርጅቶችና የአጋር ሀገራት ተወካዮችም በትግራይ ክልል ዳግም የተጀመረውን የDDR ሂደት በማድነቅ፣ ለሀገራዊው የDDR ፕሮግራም ስኬታማነት እያደረጉት ያለውን ሁሉን አቀፍ ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
በኢንቲሃድ አብራር
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: