የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን አምበል እና የአሜሪካው ዲሲ ፓወር የፊት መስመር ተጫዋች ሎዛ አበራ፣ የዲሲ ፓወር የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን አዲስ ታሪክ ከፃፈች በኋላ ከኢቲቪ ስፖርት ጋር በነበራት ቆይታ ስለ ክለብ ስኬቷ፣ ስለ ፕሮፌሽናል እግር ኳስ ጉዞዋ እንዲሁም ስለ ሀገር ውስጥ ሊግና ስለ ኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥታለች።
የዲሲ ፓወር የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብር
በአሜሪካ ጌይንብሪጅ ሱፐር ሊግ ከዲሲ ፓወር ጋር ድንቅ የውድድር ጊዜን እያሳለፈች የምትገኘው ሎዛ፣ የክለቡ የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ መሆን በመቻሏ የተሰማትን ደስታ ገልጻለች።
"በዲሲ ፓወር የምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆኔና ይህን ታሪክ በመሥራቴ ፈጣሪን እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ፤ ለዚህ ስኬት አብቅቶኛል። ከዚህ ጀርባ ደግሞ ክለቡን ከተቀላቀልኩበት ጊዜ ጀምሮ ያሳየሁት ያልተቋረጠ ጥረት፣ ልፋትና ቁርጠኝነት አለ" ስትል ተናግራለች። አክላም አንዲት ኢትዮጵያዊት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲህ ዓይነቱን ስኬት ስታስመዘግብ በራሷ እንድትኮራና በደከመችበት ሥራ እንድትደሰት እንዳደረጋት ገልጻለች።
የባህር ማዶ ቆይታ እና ለኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች መነሳሳት መሆን
ከአሜሪካ ጉዞዋ አስቀድሞ በማልታ እና በስዊድን ያሳለፈችውን ጊዜ ያስታወሰችው ሎዛ፣ ፕሮፌሽናል የእግር ኳስ ተሞክሮ እጅግ በርካታ ትምህርቶችንና ልምዶችን እንዳስገኘላት ጠቁማለች።
በሀገር ውስጥ ያሉ ተጫዋቾች ዕድሉን ቢያገኙ የተሻለ ውጤት እንደሚያስመዘግቡ ያላትን እምነት የገለጸችው አምበሏ፦ "ተጫዋቾች በሀገር ውስጥ ሊግ ብቻ መጫወትን ሳይሆን ወደ ውጭ ሊጎች ወጥተው መጫወትን፣ የተሻለ ዕውቀትና ልምድ አግኝተው ደግሞ ተመልሰው ሀገራቸውን የሚያኮሩበትን መንገድ ማሰብ አለባቸው። እስካሁን ጥቂት ተጫዋቾች ብቻ ብንወጣም፤ አሁን ላይ የእኔን ጨምሮ እንደ ሴናፍ፣ መሳይ እና አረጋሽ ያሉ ተጫዋቾች በውጭ ሊጎች ሲጫወቱ ማየታቸው ለሌሎች ትልቅ መነሳሳት ፈጥሯል። በርካቶች ከኢትዮጵያ ወጥተው የፕሮፌሽናል ጉዟቸውን ያሳድጋሉ የሚል ሙሉ ተስፋ አለኝ" ብላለች።
የሀገር ውስጥ የሴቶች ፕሪሚየር ሊግ አሁናዊ ገጽታ
ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የሊጉ ሻምፒዮን እንዲሁም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሆና ያሳለፈችውን ስኬታማ ጊዜ ያነሳችው ሎዛ፣ በአሁኑ ወቅት በርካታ አዳዲስ ተተኪ ተጫዋቾችና ክለቦች እየመጡ መሆኑ መልካም ቢሆንም አሁንም በቂ እንዳልሆነ አስረድታለች።
"አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ሊጉ በሚፈለገው ልክ ትኩረት አላገኘም። ውድድሩ በጥቂት ክለቦች እንደ ንግድ ባንክ፣ መቻል፣ ሐዋሳ እና መብራት ኃይል የበላይነት ብቻ የተያዘ ነው። ይህ መቀየር አለበት" ያለችው ሎዛ፣ ሁሉም ክለቦች ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን እንዳለባቸው አሳስባለች። አክላም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ሆነ ክለቦች ዘመናዊ የእግር ኳስ አሰለጣጠን፣ ወጥ የሆነ አሠራርና ፕሮፌሽናል አያያዝን በመከተል የሴቶች እግር ኳስ በየደረጃው ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶት ሊጉ እንዲያድግ መሥራት እንዳለባቸው አጽንኦት ሰጥታለች።
የሉሲዎቹ ውጤት ማሽቆልቆል እና መፍትሔዎቹ
የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን (ሉሲዎቹ) ከአፍሪካ ዋንጫ መድረክ መራቃቸውንና በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላቸው ውጤት እጅግ ደካማ መሆኑን ያመነችው አምበሏ፣ ውጤቱ እንደ ብሔራዊ ቡድን አባል ብዙ ሥራ እንደሚጠበቅባቸው አመላካች መሆኑን ገልጻለች።
ሎዛ እንደገለጸችው ዋነኛው ተግዳሮት የውድድር እጥረት ነው፦ "ብሔራዊ ቡድኑ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውድድር የሚያገኘው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ሲኖር ብቻ ነው። ከዛ ውጭ ደግሞ በየአራት ዓመቱ የሚደረገው የኦሊምፒክ ማጣሪያ አለ። ቀደም ሲል እንሳተፍበት በነበረው የሴካፋ ውድድር ላይ እንኳ መሳተፍ ካቆምን ረጅም ጊዜ ሆኖናል። ውድድርና የወዳጅነት ጨዋታዎች በበዙ ቁጥር ግን ቡድኑ የት ደረጃ ላይ እንዳለ ማወቅ፣ ቪዲዮዎችን ገምግሞ ድክመቶችን ማረም እና የተጫዋቾችን ኬሚስትሪ ማሳደግ ይቻላል።"
በተጨማሪም ተጫዋቾች ረጅሙን የውድድር ዘመን የሚያሳልፉት ክለቦቻቸው ውስጥ በመሆኑ፣ የክለቦች ጠንካራ መዋቅርና ሥርዓት መኖር ለብሔራዊ ቡድኑ መሠረት መሆኑን አስረድታለች። አሰልጣኞችም ራሳቸውን በዘመናዊ እግር ኳስ የስልጠና ዘይቤ ማዘመን እንዳለባቸው የገለጸችው ሎዛ አበራ፣ እየተደረጉ ያሉ ጥረቶች የሚደነቁ ቢሆንም አሁንም ሰፊ ሥራ እንደሚቀር ጠቁማ፣ አስፈላጊው መሠረታዊ ድጋፍና የማሻሻያ ሥራዎች ከተከናወኑ ሉሲዎች በአፍሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ መድረክ ተፎካካሪ ጠንካራ ቡድን ሆነው እንደሚገነቡ ሙሉ እምነት እንዳላት በመግለጽ ሀሳቧን አጠቃላለች።
በእሱባለው ተሾመ
አስተያየትዎን እዚህ ያስፍሩ: