አትሌት ገዛህኝ አበራ፣ ሌሊሳ ዴሲሳ እና ታምራት ቶላ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በማራቶን ለሀገራቸው የወርቅ ሜዳልያ ያመጡ አትሌቶች ናቸው፡፡
የፓሪስ ኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ አትሌት ታምራት ቶላ የወርቅ ሜዳልያ ባለቤት ከመሆኑ በተጨማሪ በኦሪገን የዓለም ሻምፒዮና የገባበት 2 ሰዓት 03 ደቂቃ 39 ሰከንድ የሻምፒዮናው ክብረ ወሰን ነው፡፡
በ20ኛው የዓለም አትሌቲስ ሻምፒዮና ዛሬ ሌሊት 7 ሰአት ከ 30 ላይ ኢትዮጵያ ሜዳለያ ታገኝበታለች ተብሎ የሚጠበቀው የወንዶች ማራቶን ይደረጋል፡፡

በተጠባቂው ውድድር አትሌት ደሬሳ ገለታ፣ ታደሰ ታከለ፣ ተስፋዩ ድሪባ ኢትዮጵያን የሚወክሉ አትሌቶች ናቸው፡፡
ከስድስት ወር በፊት ዛሬ ውድድሩ በሚደረግበተ ቶኪዮ በተደረገው የ2025 ማራቶን ከ1ኛ እስከ 3ኛ የወጡት አትሌቶች መኖራቸው የሌሊቱን ፉክክር ተጠባቂ አድርጎታል፡፡
አትሌት ታደሰ ታከለ በመጋቢት ወር የተካሄደውን የቶኪዮ ማራቶን በአንደኝት ማጠናቀቁ የሚታወስ ሲሆን ነው፡፡
ሌላኛው አትሌት ደሬሳ ገለታ 2ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል፡፡ በመድረኩ ኬንያዊው አትሌት ቪንሰንት ኪፕኬሞይ 3ኛ ወጥቶ እደነበር አይዘነጋም፡፡

ሌሊት ላይ በሚደረገው ውድድር ከ47 ሀገራት የተመረጡ 90 አትሌቶች የሚሳተፉ ሲሆን አትሌት ደሬሳ ገለታ 2 ሰዓት 02.38 ደቂቃ የግል ምርጥ ሰዓት በመያዝ ቀዳሚው ነው፡፡ ደሬሳ በ2024 የፓሪስ ኦሎምፒክ ሀገሩን በመወከል ተወዳድሮ እንደነበረትም ይታወሳል፡፡
የ3ሺ ሜትር መሰናክል ተወዳዳሪ የነበረው እና የቶኪዮ ማራቶን አሸናፊው ታደሰ ታከለም 2 ሰዓት 03.23 ደቂቃ የሆነ የግል ምርጥ ሰዓት ባለቤት ነው፡፡
በተመሳሳይ በ3ሺ ሜትር መሰናከል በተለያዩ መድረኮች የተወዳደረው አትሌት ተስፋዬ ድሪባ በዚህ ዓመት የተደረገው የባርሴሎና ማራቶን አሸናፊ ነው፡፡
በሌሊቱ ውድድር ዩጋንዳ የ2023 ዓለም ሻምፒዮና የማራቶን አሸናፊ መሆኗን ተከትሎ በአራት አትሌቶች የምትወከልም ይሆናል፡፡
በአንተነህ ሲሳይ