Search

የለሜቻ ግርማ የፓሪስ ኦሎምፒክ አስደንጋጭ ክስተት እና ዛሬ የሚጠበቀው ፍጻሜ

ሰኞ መስከረም 05, 2018 369

ይሄ ብዙዎችን ያስደነገጠ ክስተት ከተፈጠረ አንድ ዓመት ሆኖታል፡፡ ጊዜው እና ቦታው ደግሞ 2024 ፓሪስ ኦሎምፒክ ነው፡፡ 

ኢትዮጵያ የወርቅ ሜዳልያ ከምትጠብቅባቸው ርቀቶች አንደኛው በነበረው የወንዶች 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ሀገራቸውን የወከሉት አትሌት ለሜቻ ግርማ፣ ጌትነት ዋለ እና ሳሙኤል ፍሬው ማጣሪያውን በማለፍ ለፍጻሜ ደርሰዋል፡፡

አትሌት ለሜቻ ግርማ ከ2019 የዶሃ ዓለም ሻምፒዮና ጀምሮ ኢትዮጵያ ብዙም በማትታወቅበት 3 ሺህ ሜትር መሰናክል ልዩነት ፈጣሪ መሆኑን ለዓለም አሳይቷል፡፡ 

አሁን ላይ የርቀቱ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤት ጭምር ነው፡፡

ለሜቻ የዛሬ ዓመት በተደረገው የፓሪስ ኦሎምፒክ ከነበረው ዝግጅት እና ካለው ወቅታዊ ብቃት አንጻር የአሸናፊነት ቅድሚያ ግምቱን አግኝቷል፡፡ 

የፍጻሜው ውድድር ተጀመረ ለሜቻ ግርማ ከሀገሩ ልጆች ጋር በመናበብ በርቀቱ ለኢትዮጵያ መጀመርያ የሆነውን የወርቅ ሜዳልያ ለመውሰድ በጥንቃቄ መሮጡን እና መሰናክሉን መዝለል ቀጥሏል፡፡

ነገር ግን ውድድሩ ሊጠናቀቅ 300 ሜትር ሲቀር ትልቅ ግምት ያገኘው አትሌት ፍጥነቱን በሚጨምርበት ሰዓት በመሰናክሉ ተደናቅፎ ወደቀ፡፡ 

በገጠመው የጭንቅላት ጉዳትም በፍጥነት ወደ ሆስፒታል ተወሰደ፡፡ በወቅቱ አሜሪካዊው ኮሜንታተር ሌይ ዲፊ የጉዳቱን ክብደት ሲገልጽ በ40 ዓመታት የአትሌቲክስ ኮሜንታሪነት ስራዬ እንዲህ አይነት ክስተት አልተመለከትኩም ብሎ ነበር፡፡

ብዙዎች ቁመተ መለሎው ለሜቻ በፍጥነት እንዲያገግም እና ወደ ቀደመ ጥንካሬው እንዲመለስ ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

አስደንጋጭ የነበረው ሁነት መፈጠሩን ተከትሎ ኢትዮጵያም የርቀቱን ወርቅ ለማግኘት ሌላ ጊዜን እንድትጠብቅ ግድ ሆነ፡፡  

የ24 ዓመቱ አትሌት ከዚያ ክስተት ተመልሶ ሀገሩን በትልቅ መድረክ የሚወክልበት ሌላ ዕድል አግኝቷል፡፡ 

የ3 ጊዜ የዓለም አትሌቲከስ ሻምፒዮና የብር ሜዳልያ ባለቤቱ እና የአንድ ኦሎምፒክ የብር ሜዳልያ ባለ ክብሩ ለሜቻ ግርማ ዛሬ በሚደረገው የ3 ሺህ ሜትር መሰናከል ፍጻሜ ኢትዮጵያን ከሚወክሉት አንዱ ነው፡፡

ማጣሪያውን 2ኛ ሆኖ ያለፈው የዓለም ከብረ ወሰን ባለቤቱ ለሜቻ ግርማ ቀን 9 ሰዓት ከ55 ላይ ለሌላ ክብር ይፋለማል፡፡ 

16 አትሌቶች በፍጻሜው በሚሳተፉበት 3 ሺህ ሜትር መሰናከል በፓሪስ አብረውት የነበሩት አትሌት ጌትነት ዋለ እና ሳሙኤል ፍሬውም ይጠበቃሉ፡፡

ለሜቻ ግርማ በቡዳፔስት እና በኢውጂን ዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በቶኪዮ ኦሎምፒክ የብር ሜዳልያውን ሲወስድ በሦስቱም አጋጣሚዎች የቀመደው ሞሮኳዊው አትሌት ሶፊያን ኤል ባካሊ ዛሬም ትልቅ ፈተና እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡

በአንተነህ ሲሳይ