ኢትዮጵያ በአፍሪካ አህጉር የምንተማመንባት የረጅም ጊዜ ወዳጃችን ናት ሲሉ የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን ተናገሩ።
ፕሬዚዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) በሞስኮ ተቀብለው በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የተወያዩ ሲሆን፣ የተለያዩ ስምምነቶችንም ተፈራርመዋል።
“ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እንኳን ወደ ሞስኮ በሰላም መጡ፤ እዚህ ስላየሁዎት ደስተኛ ነኝ” ሲሉም ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል።
በሁለቱ ሀገራት መካከል ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቱ በ1898 (እ.አ.አ) መመሥረቱን የገለጹት ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ወዳጅነታችን በሂደት እያደገ ይገኛል፤ የንግድ ልውውጣችን እያደገ ነው” ብለዋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጋር በተደጋጋሚ ተገናኝተው እየተወያዩ መሆኑን ጠቅሰው፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሁኑ ስብሰባ ላይ ከፍተኛ የኢትዮጵያ ልዑካንን ይዘው በመገኘታቸው መደሰታቸውን ገልጸዋል።
በፈረንጆቹ 2025 መጀመሪያ ላይ የሩሲያ ልዑክ ኢትዮጵያን መጎብኘቱን እና በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ልዑካኑን በራሳቸው የተቀበሏቸው በመሆኑ ደስታቸውን ገልጸው፣ ምስጋናም አቅርበውላቸዋል።
ግንኙነታችን በእጅጉ እያደገ ነው ያሉት ፕሬዚዳንት ፑቲን፣ “የተከበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በድጋሚ እንኳን በደህና መጡ” ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በጉባኤው ላይ እንዲሳተፉ ስለጋበዟቸው እና ላደረጉላቸው ደማቅ አቀባበል ፕሬዚዳንት ፑቲንን አመስግነዋል።
ለመጨረሻ ጊዜ ካዛን ውስጥ ለብሪክስ ጉባኤ ፊት ለፊት ከተገናኙ ዓመት እየሞላው መሆኑን ጠቅሰው፣ ቀጣዩ ግንኙነታቸው በአዲስ አበባ እንደሚሆን ያላቸውን ተስፋ ገልጸውላቸዋል።
ኢትዮጵያ እና ሩሲያ እጅግ ጠንካራ የሆነ የሁለትዮሽ ግንኙነት ያላቸው ሀገራት መሆናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፥ ተመሳሳይ ታሪክ፣ ሃይማኖት እና በርካታ የፖሊሲ አቋም ይጋራሉ ብለዋል።
ኢትዮጵያ በጋራ መከባበር ላይ የተመሠረተ ትብብርን እንደምታስቀድም እና ስትራቴጂዋን የጋራ ከሆኑ ቀዳሚ ጉዳዮች ጋር እንደምታጣጥም እንዲሁም ወዳጆቿን በልማት እና በዲፕሎማሲ የበለጠ ማሳተፍ ላይ እንደምታተኩር አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ እና የሩሲያው ወዳጅነት ፕሬዚዳንቱ እንዳሉትም ዘመን ተሻጋሪ እና መልካም ቁመና ላይ ያለ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የአሁኑ ጉብኝት ደግሞ ይህንን መልካም ግንኙነት ወደበለጠ ደረጃ እንደሚያሸጋግረው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በዮናስ በድሉ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #Russia #diplomacy #Ethio_Russia