Search

ትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻሎች እየታዩ ነው፡ - ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ

ሓሙስ ጥቅምት 06, 2018 76

የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ገለጹ።
"የትምህርት ፍትሃዊነትና ጥራት ለትውልድ ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ 14ኛው ክልል አቀፍ የትምህርት ጉባዔ በጋምቤላ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በጉባዔው የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ባስተላለፉት መልዕክት፤ የሀገር እድገትና ስልጣኔ እውን የሚሆነው በሥነ-ምግባርና በክህሎት የታነፀ ትውልድ ማፍራት ሲቻል ነው።
ዘላቂ ልማትና እድገት እንዲረጋገጥ ጥራት ያለው ትምህርትን ተደራሽ በማድረግ በራሱ የሚተማመን ዜጋ መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
በዚህም ባለፉት የለውጥ ዓመታት የትምህርት ጥራትንና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ በተከናወኑ ተግባራት በተለይ በተማሪዎች ውጤት ላይ መሻሻሎች እየታዩ መሆኑን ገልጸዋል።
በጋምቤላ ክልልም በተማሪዎች ውጤት ላይ ለውጥ መኖሩን ጠቅሰው፤ የታየውን ለውጥ ይበልጥ ለማጠናከር አመራሩ በላቀ ቁርጠኝነት እንዲሰራ አስገንዝበዋል።
በክልሉ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ እየተከናወኑ ለሚገኙ ተግባራት ስኬት ሚኒስቴሩ የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዓለሚቱ ኡሞድ በክልሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በትምህርት ሽፋን የተሻለ ስኬት መመዝገቡን ገልጸው፤ ጥራትን በማረጋገጥ ረገድ ውስንነቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
በመሆኑም በክልሉ በትምህርት ሽፋን የተመዘገበውን ውጤት በጥራት ለመድገም ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ ጠንክሮ መስራት ይገባል ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።
ጉባዔው በሁለት ቀናት ቆይታው በክልሉ የ2017 የትምህርት ዘመን አፈፃፀምን በመገምገም በ2018 የትምህርት ዘመን የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እንደሚደረግ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ሃላፊ ኡኩኝ ኦኬሎ ናቸው።
የትምህርት ጉባዔው በዘርፉ ያሉትን ውስንነቶችና ጥንካሬዎችን በመለየት ለቀጣይ ስራዎች የጋራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ መሆኑም ተጠቁሟል።