Search

የትምህርት ዘመኑ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ይዘቶች ምንድን ናቸው?

ሓሙስ ጥቅምት 13, 2018 101

የ2018 ትምህርት ዘመን የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ይዘቶች ይፋ ሆነዋል፡፡
የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት፤ ተማሪዎች፣ የተማሪ ቤተሰቦች፣ መምህራንና የትምህርት አመራር ለፈተና ዝግጅት በሚያደርጉበት ወቅት ፈተና የሚሸፍናቸውን የይዘት አካባቢዎች እንዲያውቁ ይፋ አድርጓል።
ለተፈጥሮ ሳይንስ ተፈታኞች ዝግጅት የሚደረግባቸው የትምህርት ዓይነቶች፤ እንግሊዘኛ፣ ሒሳብ፣ እስኮላስቲክ አፕቲትዩድ፣ ኬሚስትሪ፣ ፊዝክስና ባዮሎጂ ናቸው።
ለማህበራዊ ሳይንስ ተፈታኞች ዝግጅት የሚደረግባቸው የትምህርት ዓይነቶች፤ እንግሊዘኛ፣ ሒሳብ፣ እስኮላስቲክ አፕቲትዩድ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊና ኢኮኖሚክስ ናቸው።
ፈተናው ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደረጃዎችን እና በተማሪው መጽሐፍ ላይ ያሉትን ሁሉንም ምዕራፎች ይሸፍናል።
ከ10ኛ – 12ኛ ክፍል ሁሉም የትምህርት ዓይነት ፈተና በአዲሱ ሥርዓተ ትምህርት መሠረት እየተዘጋጀ መሆኑ ተጠቁሟል።
የ9ኛ ክፍል ደግሞ የሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ፈተናዎች ከቀድሞውና ከአዲሱ ሥርዓተ ትምህርቶች የጋራ ይዘቶችን ብቻ አካቶ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ተመላክቷል።
ፈተናው ማንኛውም ተፈታኝ ተማሪ ከተማረው ሥርዓተ ትምህርትና ከተማሪው መጽሐፍ ላይ ብቻ ተመስርቶ እየተዘጋጀ መሆኑም ተጠቅሷል።
የፈተናው አስተዳደር በበይነ መረብና በወረቀት ጎን ለጎን የሚሰጥ ሲሆን አብዛኛው ተፈታኝ በበይነ መረብ እንዲፈተን እየተሠራ ስለመሆኑም ተገልጿል።
የትምህርት ዘመኑ የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተና ተፈታኞችም በበይነ መረብ ለመፈተን እራሳቸውን ሊያዘጋጁ እንደሚገባ ተመላክቷል።