አትሌት ቢኒያም መሃሪ በዓለም የአትሌቲክስ ኮከብ ታዳጊዎች ሽልማት የመጨረሻ እጩዎች ውስጥ ተካተተ።
ለዓመቱ ኮከብ አትሌቶች ሽልማት የታጨው ተስፋ በተጣለባቸው (ራይዚንግ ስታር) በተሰኘው ዘርፍ ነው።
ከ20 ዓመት በታች ባለው የዕድሜ ክልል የ10,000 ሜትር እና የቤት ውስጥ የ3,000 ሜትር የክብረወሰን ባለቤቱ አትሌት፤ በ5,000 ሜትር ርቀት የአምስተኛው ፈጣን ሰዓት ባለቤትም ነው።
በ2025 የቶኪዮ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ደግሞ አምስተኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።
አትሌት ቢኒያም መሃሪ በቀጣይ የውድድር ጊዜያት ኢትዮጵያን ወክሎ የተሻለ ውጤት እንደሚያመጣ ተስፋ የተጣለበት ስፖርተኛ ነው።
አትሌቱ በአሜሪካ የተካሄደውን የ2025 ዩጂን የዳይመንድ ሊግ የ10,000 ሜትር ውድድርን
በ26:43.82 በመግባት ማሸነፉ የሚታወስ ነው።
ከቢንያም በተጨማሪ በዓለም አትሌቲክስ ታዳጊዎች ሽልማት ዘርፍ የመካከለኛ ርቀት አትሌቱ ፋኑኤል ኮዌችና የ3,000 ሜትር መሠናክል ሯጩ ኤድሙንድ ሴሬም ከኬንያ ተካተዋል።
በእድሪስ አህመድ