Search

ኢትዮጵያ COP32 ጉባዔን ለማስተናገድ የሚያስችል ቁርጠኝነት እና ከፍ ያለ ዝግጁነት አላት - የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር)

ዓርብ ኅዳር 05, 2018 70

የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ከተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ስምምነት ማዕቀፍ ዋና ጸሐፊ ሳይመን ስቲል ጋር ተወያይተዋል።
በብራዚል ቤሌም እየተካሄደ ከሚገኘው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ ጎን ለጎን ነዉ ሚኒስትሯ ጉባዔውን ጨምሮ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይን ከሚመራው ማዕቀፉ ዋና ጸሐፊ ጋር ውይይት ያደረጉት።
ሚኒስትሯ ከውይይታቸው በኋላ ለኢቢሲ እንደገለፁት፥ ኢትዮጵያ 32ኛውን የዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ጉባዔ እንድታዘጋጅ በመመረጧ ዋና ፀሐፊው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ COP32 ጉባዔን የአፍሪካ ድምፅም በመሆን ጭምር እንዴት በተሳካ ሁኔታ ታስተናግድ በሚለው ላይ መወያየታቸውን የገለፁት ሚኒስትሯ፥ የእስካሁን ጉባዔ ውሳኔዎች ወደ ተግባር የሚቀየሩበት ቀጥለውም ለሚካሄዱ ጉባዔዎች ጥሩ መነሻ ሆኖ በስኬት እንዲስተናገድ መነጋገራቸውን ገልፀዋል።
ውይይቱ ኢትዮጵያም ያላትን የፓለቲካ ቁርጠኝነት ፣ከፍ ያለ ዝግጁነት ፣በአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ዙሪያ በመሪዋም ጭምር ያላትን ከፍተኛ ተነሳሽነት የገለፀችበት እንደሆነም አንስተው፣ በእኛ በኩል የቅርብ ክትትል የሚደረግበት እና በልዩ ትኩረት የሚሰራበት እንደሆነ በግልፅ አስረድተናል ብለዋል።
ቀጣይ በሚጠበቁ የአስተናጋጅነት ጉዳዮች ላይ ተነጋግረናል ያሉት ሚኒስትሯ፥ ዋና ጸሐፊው በዝግጅቱ ወቅት አብረውን የሚሰሩ የጽሕፈት ቤቱ የተለያዩ የሥራ ኃላፊዎችን አስተዋውቀውናል ፣ በጋራ ተባብሮ ስኬታማ እንዲሆን ለመስራትም መግባባት ላይ ደርሰናል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ከወዲሁ ዝግጅቷን ለመጀመር በተቃረበችበት ሰዓት የተደረገ በመሆኑ ፤ እጅግ ጠቃሚ እና አስፈላጊ ነበር ያሉት ሚኒስትሯ ቀጣይ የሚጠበቁብንን ጉዳዮች አንስቶ ለመነጋገር ዕድል የሰጠን ፍሬያማ ውይይት ነው ብለዋል።
በቀጣይ በከፍተኛ ኃላፊዎች ደረጃ ውይይቶች ይደረጋሉም ነው ያሉት።
በብራዚል ቤሌም እየተካሄደ በሚገኘው በዚሁ ጉባዔ ማጠቃለያ የኢትዮጵያ COP32 አዘጋጅነት በይፋ ይበሰራል ተብሎ ይጠበቃል።
በሀብታሙ ተክለሥላሴ