Search

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኤርትራ የቀጣናውን እንቅስቃሴዎች ከማወክ እንድትቆጠብ ጫና ሊያደርግ ይገባል - የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)

ቅዳሜ ኅዳር 06, 2018 126

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኤርትራ በአፍሪካ ቀንድ ያለውን እንቅስቃሴዎች ከማወክ እንድትቆጠብ እና ከክልላዊ ሰላም እና ውህደት ጋር የተጣጣመ ገንቢ አካሄድ እንድትከተል ጫና እንዲያደርግባት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ጥሪ አቀረቡ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጥሪውን ያቀረቡት በወቅታዊ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች እና በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዙሪያ ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት ነው። 

ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና Horn Review በጋራ ባዘጋጁት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ የቅድሚያ ትኩረቶችን በመግለጽ፣ ሀገሪቱ ለቀጣናው ሰላም እና መረጋጋት እንዲሁም ክልላዊ ትብብርን ለማሳደግ ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

ኢትዮጵያ ለክልላዊ ኢኮኖሚያዊ ውህደት ያላትን ራዕይ አፅንኦት የሰጡ ሲሆን፣ ይህም በጋራ የልማት አቅም እና የአፍሪካ ቀንድ ሕዝቦች የጋራ ዕጣ ፈንታ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ገልጸዋል።

በጎረቤት ሀገሮች መካከል የሚደረግ ውይይት እና የጋራ መግባባት የጋራ ፈተናዎችን ለመፍታት እና ዘላቂ ዕድገትን ለማፋጠን ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ  ከኤርትራ ጋር ስላላት ግንኙነት ሲናገሩ፣ ኢትዮጵያ በሉዓላዊነቷ እና በግዛት አንድነቷ ላይ ከባድ ጠብአጫሪነት እና ጥሰቶች ቢደረጉባትም፣  ሀገሪቱ ለሰላም ካላት ቁርጠኝነት አኳያ ከአፀፋ ራሷን በከፍተኛ ደረጃ መገደቧን ገልጸዋል።

ነገር ግን ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ቋሚ ሆኖ ይቀጥላል ማለት እንዳልሆነ አስምረውበታል። 

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ኤርትራ በቀጣናው ውስጥ ያሉ እንቅስቃሴዎችን ከማወክ እንድትቆጠብ እና ከክልላዊ ሰላም እና ውህደት ጋር የተጣጣመ ገንቢ አካሄድ እንድትከተል እንዲያበረታታ ሚኒስትሩ ጥሪ አቅርበዋል።

ዓለም አቀፍ አጋሮች የኤርትራ መንግሥት ለኢትዮጵያ እና ለክልሉ ያለውን የተሳሳተ ፖሊሲ አላግባብ እንዳይጠቀም እና ወደ ብሩህ እና የትብብር የወደፊት ተስፋን የሚያጭር ተጨባጭ እርምጃዎችን እንዲወስድ እንዲያበረታታ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ ከ130 ሚሊዮን በላይ ለደረሰው ሕዝቧ የኑሮ መሠረት ሊጥል የሚችል ዘላቂነት ያለው የኢኮኖሚ ዕድገቷ የሚረጋገጠው ዘላቂ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የባሕር መዳረሻ ሲኖራት ነው ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)።

ዘላቂ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ የባሕር መዳረሻ ከሌላት ኢትዮጵያ ቀጣይነት ያለው ልማቷን የሚያረጋግጥ የኢኮኖሚ ዕድገት ማምጣት አትችልም፤ በመሆኑም  የባሕር  መዳረሻ  የማግኘቱ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የኅልውና ጉዳይ ነው ብለዋል።

#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #HornAfrica #Seaaccess #Diplomacy