አሁን ላይ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል የተከሰተው ውጥረት ከኢትዮጵያ የባሕር በር መሻት ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) ገለጹ።
ሚኒስትሩ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና ሆርን ሪቪው በጋራ ባዘጋጁት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መድረክ ላይ በወቅታዊ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዮች እና በኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ዶክተር ጌዲዮን በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ በአሁኑ ጊዜ የዜና ርዕሶችን እና የማኅበራዊ ሚዲያ አስተያየቶችን በጥቂቱ በመመልከት ብቻ የአፍሪካ ቀንድ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ወቅት ውስጥ እንዳለ በግልጽ መረዳት ይቻላል።
ሁከት፣ ግጭት እና አለመተማመን ለረጅም ጊዜ የአፍሪካ ቀንድ መገለጫዎች ሆነው መቆየታቸውን እና አሁን ላይ አንድ ሰው የአፍሪካን የሰላም እና የፀጥታ ሁኔታ ቢቃኝ፣ በእያንዳንዱ ሀገር ውስጥ በተግባር ከፍተኛ ፈተናዎች መኖራቸውን እንደሚገነዝብም ጠቁመዋል።
ይህ የሆነው ታዲያ ቀጣናው ከፍተኛ የልማት አቅም እያለው እና በሰውም ሆነ በተፈጥሮ ሀብት ረገድ በእጅጉ የተቸረ ቀጣና ሆኖ ሳለ እንደሆነ ነው የገለጹት።
እንደ እርሳቸው ገለጻ፣ ቀጣናው ሰፊ የእርሻ መሬት፣ በርካታ የውኃ ሀብት፣ የበለፀጉ የማዕድን ክምችቶች እና ፈጠራን የተካኑ እና ኢንተርፕራይዝን ማሳለጥ የሚችሉ ታታሪ ሕዝቦችን የታደለ ነው።
የቀጣናው የባህል እና የሥልጣኔ ቅርስም ለጋራ ፍላጎቶች እና ለድንበር ተሻጋሪ ትብብር መሠረት የሚጥል ትልቅ ሀብት ነው።
ሚኒስትሩ በመድረኩ በአጠቃላይ ስለ አፍሪካ ቀንድ ዳሰሳ ለማድረግ ጊዜ እንደማይበቃቸው በመግለጽ፣ ትኩረታቸውን በዋናነት በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ለማድረግ እና ይህንንም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ዙሪያ ባላት ሰፊ የፖሊሲ ዕይታ ውስጥ ለማስቀመጥ መምረጣቸውን አብራርተዋል።
የኢትዮ-ኤርትራ ፋይል በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ከማይቋረጡ የችግር መዘዞች አንዱ ይመስላል ያሉት ዶክተር ጌዲዮን፣ የሁለቱ ሀገራት ጉዳይ ከ20ኛው ክፍለ ዘመን አጋማሽ ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ቀጣናውን ሲያውክ የቆየ ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።
ለ73 ዓመታት በዘለቀ ጊዜ ውስጥ ኢትዮጵያን እና ኤርትራን ያሳተፈ ፌዴሬሽን፣ ሙሉ በሙሉ መዋሐድ እና የመገንጠል ክስተቶች መታየታቸውን በአብነት አንሥተዋል።
በዚህ የአንድ ክፍለ ዘመን ሦስት አራተኛ በሚሆን ጊዜ ውስጥ፣ በርካታ ግጭቶች መካሄዳቸውንም በመግለጽ፣ የተከናወኑ የፖለቲካ ውቅር ለውጦች ዘላቂ ሰላም እና ስምምነት እንዳለመጡ ጠቁመዋል።
እ.አ.አ ከ1960ዎቹ መጀመሪያ እስከ 1991 ድረስ፣ ለ30 ዓመታት የዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት እንደነበር እና ይህ ግጭት በ1993 ካበቃ በኋላ ኤርትራ ነፃ ሀገር ሆና እስከ 1998 ድረስ ከኢትዮጵያ ጋር በአንፃራዊነት ሰላም ብትኖርም ይህ ሰላማዊ አብሮ መኖር ለአምስት ዓመታት ያህል ሳይዘልቅ በ1998 ጦርነት መጀመሩን አስታውሰዋል።
የኢትዮ-ኤርትራ የይገባኛል ጥያቄ ኮሚሽን በወቅቱ ግጭቱን ማን እንዳነሳሳው ባደረገው ምርመራ ኤርትራ ተንኳሽ መሆኗን እንዳረጋገጠም ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ ባገኛቸው መረጃዎች ላይ ባደረገው ጥናት “ማስረጃው እንደሚያሳየው እ.አ.አ ግንቦት 12/1998 ከነጋቱ 11:30 አካባቢ መደበኛ ወታደሮችን የያዘ ሁለት የኤርትራ የጦር ብርጌድ በታንኮች እና በከባድ መሣሪያዎች በመታገዝ የባድሜ ከተማን አጥቅቷል” ሲል መግለጹን አስታውሰዋል።
ኮሚሽኑ ይህንን ጥቃት እንደ ወረራ ገልጾ “ኤርትራ በወቅቱ በኢትዮጵያ ሰላማዊ አስተዳደር ሥር የነበረችውን ባድሜን ለማጥቃት እና ለመያዝ የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር አንቀጽ 2 ንዑስ አንቀጽ 4ን ጥሳለች” ሲል መደምደሙንም ገልጸዋል።
ይህ በኤርትራ ተንኳሽነት በሁለቱ ሀገራት መካከል የተቀሰቀሰው ግጭት በአልጀርስ ስምምነት እ.አ.አ ታኅሣሥ 2000 እልባት እንዳገኘም ነው የገለጹት።
የአልጀርስ ስምምነት በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን ጦርነት ቢያስቆምም፣ ግጭቱ በዘላቂነት እንዲፈታ እንዳላደረገም አንሥተዋል።
በዚህም ምክንያት ሁለቱ ሀገራት ለ18 ዓመታት (እ.አ.አ እስከ 2018 ድረስ) ሰላምም፣ ጦርነትም በሌለበት ሁኔታ የጠላትነት መንፈስ ውስጥ መቆየታቸውን ገልጸዋል።
እ.አ.አ በ2018 ኢትዮጵያ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ውጥረት ለማርገብ እና ግንኙነታቸውን ዳግም ለማደስ ቆራጥ እርምጃ መውሰዷን እና ከዚያም አልፎ ኤርትራ ከነበረችበት የመገለል ሁኔታ በማስወጣት ወደ ዓለም አቀፍ አቋም ለመመለስ ከፍተኛ ጥረት ማድረጓን አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያ በኤርትራ ላይ የተጣሉትን ዓለም አቀፍ ማዕቀቦች እንዲነሡ በመሟገትም ግንባር ቀደም ሚና መወጣቷንም ነው የጠቆሙት።
ከኢትዮጵያ በኩል እነዚህ ሁሉ በጎ ተግባራት ቢፈፀሙም፣ ዳግም የታደሰው የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ግን በኤርትራ በኩል ባለው አቋም ምክንያት በአጭር መቅረቱን አስረድተዋል።
ይሁን እንጂ ይህ የአጭር ጊዜ ተሞክሮ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ሕዝቦች በሰላም እና በስምምነት ለመኖር ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት እና ምኞት በድጋሚ ያሳዩበት ቅፅበት እንደሆነ ነው የገለጹት።
በሚያሳዝን ሁኔታ የኤርትራ መንግሥት ይህን የሕዝብ ስሜት አልተጋራም ያሉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)፣ ይህም የሀገሪቱ መንግሥት ለሰላማዊ እና ለመደበኛ የጉርብትና ግንኙነት ያለውን ጥላቻ በግልጽ የሚያሳይ እንደሆነ ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅት በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት ለሁሉም ግልጽ የሆነ እና የአፍሪካ ቀንድ ሰላም የሰፈነበት እንዲሆን ለሚፈልጉ አካላት ደግሞ ስጋትን የጫረ ነው ብለዋል።
እናም ጥያቄው "ይህ ታሪካዊ ክስተት ምን ይነግረናል?" የሚለው መሆኑን እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ወቅታዊ ውጥረት ያልተለመደ እንዳልሆነ አስምረውበታል።
ከ1960 እስከ 2025 ያለውን ጊዜ ብንመለከት ከኤርትራ ነፃነት በፊትም ሆነ በኋላ ግጭት እና ውጥረት በኤርትራ እና በኢትዮጵያ መካከል እንደ ሕግ ሆኖ የቀየ እንጂ አሁን ላይ ያለው የተለየ ክስተት አይደለም ሲሉ ሚኒስትሩ ሁኔታውን ገልጸውታል።
ይህንን አውድ እና ታሪካዊ ዳራ ማስታወስም የአሁኑን ውጥረት ጥልቅ ባልሆነ መንገድ ከመረዳት ለመቆጠብ አስፈላጊ መሆኑን አስረድታዋል።
አንዳንድ የውጭ ታዛቢዎች በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ያለው ውጥረት የሚመነጨው ኢትዮጵያ የባሕር መዳረሻ ለማግኘት ካላት መሻት እንደሆነ እንደሚናገሩ ጠቁመው፣ ነገር ግን እንደዚህ ያሉ ግምቶችን ከታሪካዊ ዳራ ጋር ለማጣጣም እንደሚያስቸግር ገልጸዋል።
ይህንን ሲያብራሩም፣ የኤርትራ መንግሥት የባሕር በር ጥያቄን ያላነሡ የቀድሞ የኢትዮጵያ መንግሥታትንም ጭምር በጠላትነት ሲመለከት እንደነበር አንሥተዋል።
ኤርትራ እ.አ.አ በ1998 በኢትዮጵያ ሉዓዊነት ላይ መጠነ ሰፊ ጦርነት የከፈተችውም የወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት የባሕር ተደራሽነት ጥያቄ ስላነሣ አልነበረም ነው ያሉት።
የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት መለስ ዜናዊ የባሕር በር ጥያቄ ሲያቀርቡ የነበሩ የፖለቲካ ኃይሎችን ሲገፉ እንደነበርም ተመዝግቦ የተቀመጠ ጉዳይ መሆኑን አንሥተዋል።
ምናልባትም የኤርትራ ነፃነት ቀንደኛ አቀንቃኝ የነበሩት ሰው (መለስ ዜናዊ) የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ መሆናቸው እንኳ የኤርትራ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የጥላቻ አቋም ከመያዝ አልገታውም ነበር ነው ያሉት።
በመሆኑም አሁን በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ውጥረት የተፈጠረው በኢትዮጵያ የባሕር በር መሻት ምክንያት ነው ብለው የሚያስቡ አካላት ከ1998-2000 የተደረገው ጦርነት “የድንበር ጦርነት ነበር” ብለው እንደገመቱት አካላት ተመሳሳይ ስህተት እየሠሩ መሆኑን ጠቁመው፤ ብዙውን ጊዜ ሁለቱን ሀገራት በሚመለከቱ ጉዳዮች በዐይን ከሚታዩት በላይ ናቸው ሲሉ ተናግረዋል።
ተከስተ ነጋሽ እና ጄቲል ትሮንቮል በ90ዎቹ መጨረሻ ላይ ስለነበረው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ባደረጉት አጠቃላይ ትንተና፣ የግጭቱ መንሥኤዎችን በተመለከተ የነበረውን ጥልቀት የሌለው ግንዛቤን መተቸታቸውን ዶክተር ጌዲዮን አንሥተዋል።
ሁለቱ ሰዎች ጦርነቱን ለመረዳት ባደረጉት ጥረት፣ ውስብስብ የሆኑ የኢኮኖሚ፣ የታሪክ እና የባህል ጉዳዮችን መዘርዘራቸውን ነው የጠቆሙት።
እንደ ተመራማሪዎቹ ድምዳሜ፣ በወቅቱ የነበረውን ግጭት መንሥኤዎች በጥልቀት አለመተንተናቸው ጦርነቱን ለመግታት የተደረጉት ጥረቶች ውጤታማ እንዳይሆኑ አድርጓል።
ባድሜ ከተማን በተመለከተ የተነሣው የድንበር ግጭት ለ1990ዎቹ ጦርነት መንሥኤ ሆኗል በሚል በስህተት እንደተገመተው ሁሉ፣ አሁንም አንዳንዶች የአሰብ ወደብ የሁለቱ ሀገራት የውዝግብ አንጓ እና በሁለቱ ሀገሮች መካከል ለተፈጠረው ውጥረት መንሥኤ መሆኑን በተሳሳተ መንገድ እንደሚያስቡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
እንዲህ ዓይነቱ ግምት፣ ነገሮችን ከልክ ባለፈ መልኩ ማቃለል እንደሚሆን እና እውነታው ትክክለኛ ግንዛቤ እንዳያገኝ እንቅፋት እንደሚሆን ጠቁመዋል።
እንዲህ ዓይነቱ የተሳሳተ ምርመራ ደግሞ የተሳሳቱ እና ጠቃሚ ያልሆኑ መፍትሔችን ሊያስከትል ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ይልቁንም ችግሩን ለመፍታት ከመሞከራችን በፊት ስለ ችግሩ ትክክለኛ እና ጥልቅ ግንዛቤ ማግኘት አስፈላጊ ነው ብለዋል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር)።
በዮናስ በድሉ
#EBC #ebcdotstream #Ethiopia #HornAfrica #Seaaccess #Diplomacy