ግንባታው እየተከናወነለት ያለው የባሕርዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም 52 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ነው፡፡
ስታዲየሙ 23 የሚደርሱ የተለያዩ የስፖርት አይነቶችን ማስተናገድ እንዲችል ተደርጎ መሠራቱም ተመላክቷል።

በአሁኑ ወቅት በስታዲየሙ ወንበሮችን የመግጠም እና የሣር ንጣፍ ሥራዎች የተጠናቀቁ ሲሆን ሌሎች ቀሪ መሠረተ ልማቶችን የማሟላት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑም ተጠቁሟል።
የስታዲየሙ አጠቃላይ የግንባታ ሥራው ተጠናቅቆ ለአገልግሎት ክፍት ሲደረግም ከመደበኛ ከውድድሮች ባሻገር፣ ለከተማዋ ወጣቶችና ለማህበረሰቡ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ታሳቢ ተደርጓል።
የባሕልና ስፖርት ሚኒስትር ሸዊት ሻንካን ጨምሮ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የጤና ማህበራዊ ጉዳዮች ባህልና ስፖርት ቋሚ ኮሚቴ አባላት፣ በባሕርዳር ከተማ በባህልና ስፖርት ሴክተር የተሰሩ የልማት ሥራዎችን ምልከታ እያደረጉ ነው።

በከተማዋ ምልከታ እየተደረገባቸው ከሚገኙት የልማት ሥራዎች መካከል የባሕር ዳር ዓለም አቀፍ ስታዲየም አንዱ ሲሆን ስታድዮሙ ዓለም አቀፍ ደረጃዎችን ጠብቆ መገንባቱ በምልከታው ወቅት ተገልጿል።
በመስክ ምልከታው ከስታዲዮሙ በተጨማሪም በከተማዋ የሚገኙ የዕደ ጥበብ ማዕከላት በባሕርዳር ዩኒቨርስቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ውስጥ ምልከታ ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል።
በሳሙኤል ወርቅአየሁ