25ኛ ዓመቱን እያከበረ የሚገኘው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ከቀጣይ ዓመት ጀምሮ ከባንክ ኦፍ አሜሪካ ጋር ለ5 ዓመት የሚያቆየውን ስምምነት ተፈራርሟል።
የአጋርነት ስምምነቱ ዋናውን የ10 ኪሎ ሜትር እና የህጻናት እንዲሁም የሴቶች 5 ኪሎ ሜትር ውድድርን ያካተተ መሆኑ ይፋ ተደርጓል።

የባንክ ኦፍ አሜሪካ የዓለም አቀፍ ገበያ እና አጋርነት ባለሙያ የሆኑት ብራድፎርድ ሮስ፥ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ማህበረሰቡ ውስጥ የፈጠረው ትልቅ አስተዋጽኦ ወደ ኢትዮጵያ እንድንመጣ አድርጎናል ብለዋል።
ባንኩ ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር የመሥራት ዕድል በማግኘቱ ደስተኛ መሆኑን የተናገሩት ብራድፎርድ ሮስ፤ በአፍሪካ በስፖርት ዙሪያ ብቻ ያለው GDP በትልቁ እየጨመረ በመምጣቱ ከዚህ ዕድገት ለመቋደስ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱን ገልጸዋል።
በኃይሌ ግራንድ በተካሄው የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ 25ኛ ዓመት የምስረታ በዓል ላይ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች፣ የቀድሞ እና የአሁን አትሌቶች እንዲሁም የውጭ ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።
በመርሐ ግብሩ ላይ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ባለፉት በርካታ ዓመታት አብረውት ሲሠሩ ለቆዩ ተቋማት እውቅና ሰጥቷል።
የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና ሌሎች በርካታ ተቋማት በመርሐ ግብሩ እውቅና ተሰጥቷቸዋል።

የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሠራተኞችም ለውድድሩ መስራች እና ባለቤት ሻለቃ አትሌት ኃይሌ ገ/ሥላሴ ሽልማት አበርክተውለታል።
55 ሺህ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የፊታችን እሁድ ለ25ኛ ጊዜ የሚካሄድ ይሆናል።
በአንተነህ ሲሳይ
#ebcdotstream #greatethiopianrun #bankofamerica #25thanniversary