ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለንባብ ያበቋቸው "የመደመር" ተከታታይ መጽሐፍት ከዕውቀት ምንጭነት አልፈው የልማት መሰረት፣ የግንባታ ጡብ ሆነዋል።
የመጽሐፍቱ ሽያጭ ገቢ ዛሬ በኢትዮጵያ የተለያዩ አቅጣጫዎች ትምህርት ቤት፣ ቤተ መጻሕፍትና የስፖርት ማዘውተሪያዎች እንዲሁም ሙዚየም እና በርካታ የልማት ሥራዎች ላይ ውሏል።
የመደመር እሳቤ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ የሀገርን አቅም የማስተባበር ጉዳይ ላይ ያተኩራል። በተግባር ደግሞ የመጽሐፍቱ ሽያጭ ይህንኑ እሳቤ በሚያንጸባርቅ መልኩ፤ የተገኘውን ሀብት ወደ ሕዝብ መልሶ በማፍሰስ "ከሕዝብ ለሕዝብ" የሚለውን መርህ ህያው አድርጎታል።
የመጽሐፍቱ የልማት ዐሻራ አዲስ አበባ ላይ ብቻ አልቆመም፤ ክልሎችንም አዳርሷል። "የመደመር ትውልድ" መጽሐፍ ሲሸጥ፣ ገቢው በኢትዮጵያ አራቱም ማዕዘናት የልማት ዐሻራዎችን አሳርፏል።
የመጀመሪያው የመደመር መጽሐፍ ለገበያ ሲቀርብ፣ ከሽያጩ የተገኘው 110 ሚሊዮን ብር በቀዳማዊት እመቤት ጽህፈት ቤት በኩል ለትውልድ ግንባታ ዋለ። ስያሜያቸው እንደ ተግባራቸው ብርሃን የሆኑት "መሰረተ ብርሃን"፣ "ኢፋ ሮጲ"፣ "ኢፋ ነዲ ጊቤ" እና ሌሎችም ትምህርት ቤቶች ከዚህ ገቢ ተገነቡ።

ለልዩ ድጋፍ ፈላጊዎች ተስፋ የሆነው የዲቦራ ፋውንዴሽን ትምህርት ቤትም የዚህ በጎ ተግባር ዐሻራ አርፎበታል። ይህ የሚያሳየው መጽሐፉ ያቀበለው ሃሳብ ብቻ ሳይሆን፣ የቀረጸው ትውልድ መሆኑን ነው።
በምስራቅ የሀገሪቱ ክፍል፣ ሐረር በኢኮ ፓርክ አረንጓዴ ልብሷን ስታደምቅ፤ በሶማሊ ክልል ወጣቶች ጤናቸውን የሚጠብቁበት መለስተኛ ስታዲየሞች እየተገነቡ ነው።
ወደ ደቡብ ምዕራብ ሲዘለቅ፣ ቦንጋ ላይ "የመደመር ትውልድ ቤተ-መጻሕፍት" ተገንብቶ የእውቀት ማዕድ ሲዘረጋ፤ ጋምቤላም የሕዝብ ቤተ-መጻሕፍትን አግኝታለች።
አሶሳ ኅዳሴ ሙዚየምን ድሬዳዋ የእመርታ ቤተ-መጻሕፍትን ሲያገኙ፣ በታሪክ እና ቅርስ ዘርፍ ደግሞ የማዕከላዊ ኢትዮጵያው የጢያ መካነ ቅርስ እና የአፋር ክልሉ የሱልጣን አሊሚራህ ሐንፍሬ ቤተ መንግስት እድሳት ታሪክን ከነገ ጋር የሚያስተሳስሩ የቱሪዝም ፕሮጀክቶች ሆነዋል።

የመዲናዋ ወጣቶችም የዚህ በረከት ተቋዳሽ ናቸው። የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን እንደሚገልጹት፣ በከተማዋ ሁሉም ክፍለ ከተሞች ከሽያጩ በተገኘ ገቢ የስፖርት ማዘውተሪያዎች እና የህጻናት መጫወቻዎች ተገንብተዋል።
ይህም ወጣቱ ጊዜውን በአግባቡ እንዲጠቀምና ጤናማ ትውልድ እንዲፈጠር የጎላ ሚና ይጫወታል ይላሉ።
እነዚህ ፕሮጀክቶች እንደሚያሳዩት፣ የመደመር መጽሐፍት ፋይዳ ዘርፈ ብዙ ነው ያሉት አቶ በላይ፤ በአንድ በኩል ለኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞና ለብልጽግና የሚሆን የመፍትሔ ሃሳብን በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ሲያቀብሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የሽያጭ ገቢያቸው የትምህርት፣ የጤና እና የቱሪዝም መሰረተ ልማት ሆኖ መሬት ላይ ማረፉን አንስተዋል።
ለሀገር ሁለንተናዊ እድገት ትልቅ ተምሳሌት በመሆኑን ቃላት ወደ ተግባር፣ ሃሳብ ወደ ግንባታ ሲቀየር ማየትም አስደሳች መሆኑን በርካቶች ይገልፃሉ።
በቢታኒያ ሲሳይ