ጥልቅ የሆነ የመልማት ፍላጎታችንን በማሳካት ሀገራችንን ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማድረስ በሁሉም ተቋማት ዘንድ ጥራትን እና ተወዳዳሪነትን ቁልፍ ተግባር አድርጎ መያዝ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) ገለጹ።
12ኛው ዙር አገር አቀፍ የጥራት ሽልማት ሥነሥርዓት ፕሬዚዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ በተገኙበት በብሔራዊ ቤተመንግሥት እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት የቦርድ ሰብሳቢ ሳሙኤል ክፍሌ (ዶ/ር) በሥነሥርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፥ አምራች እና አገልግሎት ሰጪዎችን ጨምሮ ሁሉም ድርጅቶች ጥራትን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪነትን ታሳቢ ማድረግ ይገባቸዋል ብለዋል።
የጥራት ሽልማት ለአንድ ሀገር ዕድገት ትልቅ ሚና ይጫወታል ያሉት ዶ/ር ሳሙኤል፤ የተለያዩ የአፈፃፀም ስኬቶች ለሽልማቱ እንደ መለኪያ መስፈርት መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
ከእነዚህም መካከል የሥራ ዕድል ፈጠራ፣ የተኪ ምርት መጠን፣ የውጭ ምንዛሬ ገቢ፣ የግብር እና ታክስ አበርክቶ፣ የማኅበረሰብ ልማት፣ ማኅበራዊ ኃላፊነትን መወጣት የሚሉት ይገኙበታል።
ከ18 ዓመታት በፊት የተመሠረተው የኢትዮጵያ ጥራት ሽልማት ድርጅት ጥራትን እና ተወዳዳሪነትን በሀገሪቱ ባህል እንዲሆን በመሥራት ትልቅ ለውጥ እያመጣ ያለ ተቋም መሆኑንም ገልጸዋል።
በመሐመድ ፊጣሞ
#ebcdotstream #Ethiopia #QualityAward #EQA