የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን፤ የከተማዋን የኢኮኖሚ ሽግግር በማፋጠን እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረጉ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ማዕከላትን ጎበኙ።
ጉብኝቱ የአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ያለውን አቅም ለመገምገም እና አስተዳደሩ እየሰጠ ያለውን ድጋፍ ውጤታማነት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ከንቲባ አዳነች ተናግረዋል፡፡
ከንቲባዋ አያይዘውም፤ የአምራች ኢንዱስትሪው በልዩ ትኩረት እየተሰራበት መሆኑን ጠቅሰው፣ የተለያዩ ዘርፎችን በማስተሳሰር፣ ኢንዱስትሪው ለኢኮኖሚ ዕድገት ያለውን አስተዋፅኦ በማሳደግ ረገድ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ግብዓትና ድጋፍ ማድረጉን እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል፡፡

በጎበኘናቸው ኢንዱስትሪዎች የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች፣ የምርት ሂደት በተለይም በተኪ ምርት እና ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን በማምረት ረገድ እያከናወኑት ያለው ሥራ አበረታች ነው ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
የአምራቾች ዘርፉን ተወዳዳሪነት ለማሳደግ በፈጠራና በቴክኖሎጂ ታግዞ የጥራት ደረጃውን ማሻሻል እንደሚገባም አመላክተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነባር ኢንዱስትሪዎችን በማጎልበት እንዲሁም አዳዲሶችን በማበረታታት የኢንዱስትሪ ሽግግሩን ቀጣይነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራ መሆኑም ተገልጿል።
በመሀመድ አልቃድር