በአፋር ክልል በተፈጥሮ ሀብቷ የምትታወቀው አፍዴራ ወረዳ በብዙዎች ዘንድ የምትታወሰው በጨው ምርቷ ነው።
በኤርታሌ እሳተ ገሞራ ምክንያት በርካታ ቱሪስቶች የሚጎበኟት አፍዴራ፤ ከጨው ሀብቷ በተጨማሪ የተለያዩ የሰብል ምርቶች የሚገኙባትም ናት።
አቶ መሐመድ ሙራሌ በአፍዴራ ወረዳ ኩስረወድ ቀበሌ፣ አብደሎሊ መንደር ነዋሪ ናቸው።
ላለፉት 9 ዓመታት በዚህ መንደር የተለያዩ ሰብሎችን እያለሙ እንደሚገኙ ነው አቶ መሐመድ የሚናገሩት።
በአካባቢው ለመስኖ የሚሆን ወንዝ ባይኖርም፣ አንድ ጊዜ ከሚንዘንበው ዝናብ በሚገኘው ውኃ ብቻ ሰብል እንደሚያመርቱ ገልጸዋል።

አፈሩ ለም በመሆኑ ለአንድ ጊዜ ዝናብ ካገኘ በኋላ እርጥበቱን ይዞ ለብዙ ጊዜ ያቆያል። ይህም ከሰብሎቻቸው ጥሩ ምርት ለመሰብሰብ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።
አሁን ላይ አቶ መሐመድን ጨምሮ 30 የሚሆኑ የመንደሩ ከፊል አርሶ አደሮች በማኅበር ተደራጅተው ከ30 ሄክታር በላይ ሰብል እያመረቱ ይገኛሉ።
አርሶ አደሮቹ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ሃብሃብ፣ ሽንኩርት እና ሌሎች ምርቶችን ያመርታሉ።
አካባቢው በከርሰ ምድር ውኃ የታደለ ስለሆነ መንግሥት በዚህ ረገድ ድጋፍ ቢያደርግላቸው ለግብርና ምቹ ከሆነው መሬት የተሻለ ምርት ማግኘት እንደሚቻል ያምናሉ።
ባለፈው ዓመት በግል ጥረታቸው 60 ኩንታል የማሽላ ምርት መሰብሰብ የቻሉት እኚህ ታታሪ አባት፤ በዘንድሮው ዓመት የመንደሩን ነዋሪዎች በማደራጀት በሠሩት ሥራ የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
በሁሴን መሐመድ
#ebcdotstream #Afar #agriculture