Search

በዓለም መድረክ ፍሬ እያፈራ ያለው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ

ሰኞ ኅዳር 22, 2018 125

የኢትዮጵያ መንግሥት ከንጉሱ ዘመን አንስቶ በዘመናዊ አሰራር የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ለማሳደግ የተለያዩ ርዕዮተ ዓለማዊ መሠረት ያላቸውን የኢኮኖሚ ሞዴሎች ሲከተል ቆይቷል።
በእነዚህ ያለፉት ዓመታት አበረታች ውጤቶች ቢያዩም የኢኮኖሚ ዕቅዶቹ ዘላቂና መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት አቅም ያጠራቸው እንደነበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በመደመር መንግሥት መጽሐፍ ላይ በሰፊው አብራርተዋል።
በተለይም ባለፉት ዓመታት ተከስቶ የነበረው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት እና የኢኮኖሚው መቀዛቀዝ፣ ሀገሪቱ አዲስና አሳታፊ የኢኮኖሚ ፍኖተ ካርታ እንድትከተል አስገድዷታል።
ይህንን ክፍተት ለመሙላት ከለውጡ በኋላ በመንግሥት የተጀመረው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ በመጀመሪያው ምዕራፍ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባቶችን በማረም ረገድ ውጤት ታይቶበታል፤ አሁን ላይ ዓለም አቀፍ ትብብርን ባጠናከረ መንገድ ወደ ሁለተኛው የኢኮኖሚ ሪፎርም ተሸጋግሯል።
ይህንን የኢኮኖሚ ሪፎርም ዓለም አቀፋዊ ተቀባይነት ለማጎልበት እና ሀብት ለማሰባሰብ በርካታ የዲፕሎማሲና ፋይናንስ ተኮር ውይይቶች ተካሂደዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በተካሄደው የቡድን 20 ጉባኤ ላይ ከተለያዩ የዓለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር ኢኮኖሚውን ለማሳደግ የሚረዱ ውጤታማ ውይይቶችን አድርገዋል።
በተለይም ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ዋና ዳይሬክተር ክሪስታሊና ጂኦርጂየቫ ጋር በዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ ተግዳሮቶች እና በኢትዮጵያ የሪፎርም ሂደት ላይ ያተኮረ ፍሬያማ ውይይቶችን አድርገውም ነበር።
ዳይሬክተሯ የኢትዮጵያን የሪፎርም ርምጃ ያደነቁ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ተቋሙ ለሚያደርገው ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ምስጋና በማቅረብ፣ መንግሥት ከሽግግሩ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ጫናዎችን ለመቋቋም እና አካታች ዕድገትን ለማረጋገጥ ያለውን ቁርጠኛነት አረጋግጠዋል።
በተመሳሳይ መልኩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ጋር በተደረገው ምክክር፣ ኢትዮጵያ የዘላቂ ልማት ግቦችን ለማሳካት በምታደርገው ጥረት ዙሪያ የተቋሙን ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚያጠናክር ነበር።
በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዓለም ባንክ ፕሬዚዳንት አጃይ ባንጋ እና ከአውሮፓ ኅብረት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አንቶኒዮ ኮስታ ጋር፣ የፋይናንስ አቅርቦትን ማሳደግ በሚቻልባቸው መንገዶች ላይ መክረዋል።
በአፍሪካ ደረጃም ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት ዶክተር ሲድ ኡልድ ታህ ጋር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያደረጉት ውይይት፣ ኢትዮጵያ በአህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ የባለብዙ ወገን መድረኮች ያላትን ተሰሚነት ከፍ ያደረገ ነው።
እነዚህ በከፍተኛ ደረጃ የሚደረጉ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቶች ፖለቲካዊ ትርጉም ብቻ ሳይሆን፣ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ናቸው።
ጠንካራ ዓለም አቀፍ ትብብር እና የልማት አጋሮች ድጋፍ፣ ለኢትዮጵያ ግዙፍ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን ለማፋጠን እና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን (FDI) ለመሳብ እንደ ወሳኝ ግብዓት ያገለግላሉ።
ከመሪዎቹ ጋር የተደረጉት ስምምነቶች የሀገርን የውስጥ አቅም በውጭ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ በማጠናከር፣ ኢትዮጵያ የጀመረችውን የልማት ጉዞ በጽኑ መሰረት ላይ ለማቆም የሚያስችል አቅም ይፈጥራሉ።
በመሆኑም፣ መንግሥት የዘረጋው የዲፕሎማሲ መረብ፣ የኢኮኖሚ ሪፎርሙን ከተግዳሮቶች አሻግሮ ለዜጎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚውልበትን ምቹ ሁኔታ በመፍጠር ረገድ ትልቅ ሚና ይጫወታል።
በጌትነት ተስፋማርያም