Search

ዲፕሎማሲያዊ ድል የተገኘበት መድረክ

ማክሰኞ ኅዳር 23, 2018 71

ኢትዮጵያ ለብዙ ዓመታት የቆየ ጠንካራ የዲፕሎማሲ መሰረት የነበራ ሀገር ናት፡፡

ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲ ታሪኳ የአፍሪካን የጋራ አቋም በማንፀባረቅና የጋራ ድምፅ በማስተጋባት፤ የአፍሪካ ወካይ ድምፅ መሪ ሆና በመቆም ትታወቃለች፡፡

በውጭ ጉዳይ ኢንስቲትዩት የኤዥያ ፣ፓስፊክ እና መካከለኛው ምስራቅ ከፍተኛ አማካሪ አቶ አንተነህ ጌታቸው ከኢቢሲ ዳጉ ፕሮግራም ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበራት የዲፕሎማሲ ታሪክ አሁን ለደረሰችበት የዲፕሎማሲ ስኬት አግዟታል ብለዋል፡፡

በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ በተካሄደው የቡድን 20 ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ መሳተፏ ለዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እና በዓለም ላይ ያላትን ተሰሚነት ማጉላት የቻለ መሆኑን አቶ አንተነህ ተናግረዋል፡፡

የቡድን 20 ሀገራት ስብሰባ 80 በመቶ በላይ የዓለምን ኢኮኖሚ የሚያንቀሳቅሱ ሀገራት የሚሰባሰቡበት እንደመሆኑ ለኢትዮጵያ ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ፣ የፀጥታ ትብብርን ለማጠናከር እንዲሁም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ሪፎርም እና የዕዳ ሽግሽግ ጥያቄዎችን ለማሳካት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት አመላክተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በፀጥታ እና ደህንነትም ሆነ በአየር ንብረት ለውጥ ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ በመድረኩ የራሷንም ሆነ የአፍሪካን ድምፅ ማሰማት መቻሏን አቶ አንተነህ ገልፀዋል፡፡

ይህም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን የልማት እና የፋይናንስ ትብብርን እንዲሁም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

የውጭ ጉዳይ እና ደህንነት መምህርና ተመራማሪ ቃለአብ ታደሰ በበኩላቸው፤ በደቡብ አፍሪካ በተካሔደው መድረክ ኢትዮጵያ የሁለትዮሽ እና ባለ ብዙ ወገን ጉዳይን አንስታ የአፍሪካን የጋራ ድምፅ መስተጋባቷን ገልፀዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) ከቡድን 20 ጉባኤ ጎን ለጎን 16 በላይ የሀገራት መሪዎች ጋር እንዲሁም እንደ አይ ኤም ኤፍ፣ አለም ባንክ እና የአፍሪካ ልማት ባንክ ኃላፊዎች ጋርም መምከራቸውን ተመራማሪው ተናግረዋል፡፡

በውይይቶችም በኢኮኖሚ መረጋጋት፣ በተደረጉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች የመጡ አመርቂ ውጤቶች፣ በኢንቨስትመንት የበለጠ የተሳሰረ ግንኙነት ለመፍጠር እና የንግድ ልውውጦችን ለማሳደግ ብሎም መጠናከር የሚገባቸው ጉዳዮች መዳሰሳቸውን ጠቁመው፤ ይህም በጥቅሉ ለኢትዮጵያ ዲፕሎማሲያዊ ድል ያጎናፀፈ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በንፍታሌም እንግዳወርቅ

#Ebc #Ebcdotstream #Ethiopia #G20Summit #Diplomacy #Bilateral