Search

አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) የሹመት ደብዳቤያቸውን ለፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያ አቀረቡ

ማክሰኞ ኅዳር 23, 2018 73

በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢፌዲሪ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ጀማል በከር (ዶ/ር) የሹመት ደብዳቤያቸውን ለተባበሩት አረብ ኢሜሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን በቃስር አል ዋታን ቤተ መንግስት በተካሄደ ስነ ስርዓት አቅርበዋል።

በሥነ ስርዓቱ ላይ አምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) ከፕሬዝዳንት ታየ አጽቀ ሥላሴ እና ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች ፕሬዝዳንት ሼክ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የተላከውን ወንድማዊ ሠላምታ እና የመልካም ምኞት መልዕክት አድርሰዋል፡፡ 

አምባሳደሩ በዚሁ ወቅት ለተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች 54ኛ የምስረታ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ሲሉ ለፕሬዝዳንቱና ለመላው የአገሪቱ ህዝብ የመልካም ምኞት መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

በሁለቱ ወዳጅ አገራት መካከል ያለውን ስትራቴጂካዊ አጋርነት ለማጠናከር በተለይም በንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በሎጂስቲክስና በመሰረተ ልማት፣ በቴክኖሎጂ እና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ወደ አዲስ ከፍታ ለማድረስ በቁርጠኛነት እንደሚሰሩም አምባሳደሩ አረጋግጠዋል።

ፕሬዝዳንት ሼክ መሀመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን የሹመት ደብዳቤውን በደስታ ተቀብለው፤ ለአምባሳደር ጀማል በከር (ዶ/ር) መልካም የስራ ዘመን እንዲሆንላቸው ያላቸውን ምኞት መግለጻቸውን በተባበሩት ዐረብ ኤምሬቶች የኢትዮጵያ ኤምባሲ ለኢቢሲ በላከው መረጃ አመልክቷል።

አገራቸው ከኢትዮጵያ ጋር ላላት ወዳጅነት ልዩ ቦታ እንደምትሰጥም ገልጸው፤ ኢትዮጵያ ብልጽግናን እንዲሁም ቀጠናዊ የኢኮኖሚ ውህደትን ለማረጋገጥ የምታደርገውን ጥረት መደገፋቸውን እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።