የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ከደረሰኝ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ በግብር ከፋዮች ከባለሙያዎች ሥነ-ምግባር ጉድለት ጋር በማያያዝ የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በተሟላ ደረጃ ለመቅረፍ የሚያስችል ቴክኖሎጂ አልምቶ ወደ ተግባር ማሸጋገሩ ተገለጸ።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ፥ በደረሰኝ ቁጥጥር ባለሙያዎች ዩኒፍርም ላይ በተገጠመ የካሜራ ቴክኖሎጂ፣ ቢሮው ፍትሃዊ የገቢ አሰባሰብ ለመዘርጋት በቀየሳቸው አሠራሮች፣ በቅሬታ አቀራረብ እና አፈታት እንዲሁም በተቋሙ የሪፎርም ሥራዎች ትግበራ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቢሮው ለከተማችን ልማት የሚውል ገቢ በፍትሃዊነት ለመሰብሰብ እንዲሁም በግብር ከፋዮች ከታክስ ውሳኔ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎች ለመፍታት 24 አሠራሮች በመዘርጋት ወደ ተግባር ማሸጋገር መቻሉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል።

ከዚህ አኳያ ቢሮው የደረሰኝ የቁጥጥር ተግባራት ከሌብነትና ብልሹ አሠራር የፀዳ ለማድረግ እንደሚያስችል የታመነበት የካሜራ ቴክኖሎጂ ከኢንሳ ጋር በመቀናጀት አልምቶ ወደ ተግባር ማሸጋገሩን ገልጸዋል።
ቴክኖሎጂው የቁጥጥር ባለሙያዎች ቁጥጥራቸውን በድምፅ በምስል በመቅረፅ በቀጥታ ለዋና መሥሪያ ቤት እና ለቅርንጫፎች እንደሚልክም አብራርተዋል።
ይህም በግብር ከፋዮች "አለአግባብ እና ኢ-ፍትሐዊ በሆነ ሁኔታ ቅጣት ተጣለብን፣ የቁጥጥር ባለሙያዎች ጉቦ እየተቀበሉ ነው" የሚሉ ቅሬታዎችን በማጣራት ትክክለኛ ምላሽ ለመስጠት እና የተጠያቂነት ሥርዓት ለማስፈን እንደሚያስችል ገልጸዋል።

የቁጥጥር ባለሙያዎች በተፈቀደላቸው አካባቢ ብቻ ቁጥጥር እያደረጉ ስለመሆኑ እንዲሁም ከግብር ከፋዮች ጋር ያላቸው ግንኙነት በድምጽ እና በምስል በመቅረጽ በዋና መሥሪያ ቤት ለመከታተል የሚያስችል እንደሆነም አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ቢሮው ከደረሰኝ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ የበር ለበር፣ የመጋዘን እና የደረቅ ጭነት ተሸከርካሪዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በከተማዋ በሁሉም አካባቢዎች ቁጥጥሩን አጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።
ከቅሬታ አቀራረብ እና አፈታት ጋር በተያያዘም ቢሮው በተለይም በግብር ከፋዮች ከታክስ ውሳኔ ላይ የቀረቡ ቅሬታዎች በቅሬታ የሥራ ክፍሉ በማጣራት ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው፣ በዚህም ባለፈው ዓመት ብቻ 63 በመቶ የሚደርሱ የታክስ ቅሬታዎች በማሻሻል ውሳኔ መስጠቱን ተናግረዋል።
በሌላ በኩልም በተለያዩ ምክንያቶች ዝቅ ብለው ተወስነው የነበሩ የታክስ ውሳኔዎች በኦዲት ጥራት አረጋጋጭ የሥራ ክፍሉ ዳግም ኦዲት በማድረግ እና በማሻሻል የመንግሥት ጥቅም ለማስጠበቅ መቻሉ በጋዜጣዊ መግለጫው አመላክተዋል ።
በቅርቡ በቢሮው በሚሰጡ የታክስ ውሳኔ ቅሬታ ውሳኔዎች ያልረካ ግብር ከፋይ እንዲሁም ከአገልግሎት አሰጣጥ እና ከባለሙያዎች ሥነ ምግባር ጋር በተያያዘ ቅሬታ ያለው ማንኛውም ግብር ከፋይ ቅሬታውን በከንቲባ ጽ/ቤት ለተቋቋመ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ፊት በማቅረብ እንዲፈታለት ለማድረግ የሚያስችል አሠራር የተመቻቸ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፍትሃዊነት ከሚሰበስበው ገቢ 72 ከመቶው ለከተማዋ ሁለንተናዊ ልማት እና ብልፅግና፣ ለሰው ተኮርና ድህነት ቅነሳ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ለኮሪደር ልማት ስራዎች በቀጥታ እያዋለ ይገኛል ብለዋል አቶ ቢኒያም።
የከተማ አስተዳደሩ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ግብር ከፋዮች እቃዎችን ሲሸጡ እና ሲገዙ በደረሰኝ ብቻ እንዲፈፅሙ፣ እንዲሁም ሕብረተሰቡ እቃዎች እና አገልግሎቶች ሲገዛ ደረሰኝ በመቀበል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል።
#ebcdotstream #addisababa #revenue #tax